የማያቋርጥ ታሪክ የሚሰራባት ሀገር
(By Fanowedy Samara)
Comment on fanowedy@gmail.com
የሰው ልጅ መገኛና የበርካታ ታሪካዊ አሻራዎች መዳረሻ እንድሁም የጥንታዊ ስልጣኔ መፈለቂያ፤ የበረዶ አክሊል ከደፋው የራስ ዳሽን ተራራ እስከ የከርሰ-ምድሯ በረከት የሆነችው ዳሉል እንዲሁም ከሃይቆች ስብስቡ ታላቁ የምስራቅ አፍሪካ ስምጥ ሸለቆ እስከ ዕረፍት የለሹ አርታእሌ እና ሌሎች መሰል ተፈጥሮኣዊ ትውፍቶች ባለቤት ሀገር-ኢትዮጵያ።
እገሪቱ የየራሳቸው ታሪክ፣ቋንቋ፣ ባህልና ልምድ፣ እምነትና ሃይማኖት ወዘተ ያላቸው ከ80 በላይ የሆኑ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ተስማምተውና ተከባብረው በመፈቃቀድ ላይ የተመሰረተ አንድነታቸው ጠብቀው ለዘመናት አብረው የኖሩባትና የሚኖሩባት የመቻቻል ተምሳሌትም ናት።
እነዚህ በመቻቻል የተጠመቁ፣ ለአንድነታቸው የተዋደቁና የሚዋደቁ፣ ለባእድ ሃይሎች የማይበገሩ የነፃነት አባቶች ኢትዮጵያውያውያን የበርካታ ያልተነገሩ ታሪኮች ባለቤቶች ናቸው። ኢትዮጵያና ታሪክ አንዲሁም ታሪክና ኢትዮጵያም ከማንኛውም ህዝብ በላይ ቀድመው እንደሚተዋወቁ ለማወቅ ወይም ለማስረዳት የሚፈልግ ካለ ድንቅነሽ/ሉሲን መጠቆም ብቻውን በቂ ነው። ምክንያቱ ደግሞ ታሪክ የሚባለው የሰው ልጅ ታሪክ እስከሆነ ድረስ፣ የሰው ልጅ ጥንታዊ መፍለቆያው ደግሞ የሉሷ እናት ኢትዮጵያ ናትና ብዙ ምርምር ሳያስፈልገው እዛው ሳለ በአንድ ምትሃታዊ ቃል ‘ድንቅነሽ’ ብሎ ማርጋገጥ ማለት ነው።
ኢትዮጵያውያን ከ6000 ዓመታት በፊት እንስሳትና አትክልት በማላመድ ግብሪና ጀምረው እንደነበር የታሪክ ድርሳናት ያወሳሉ። በመሆኑም እንደ ኑግ፣ሰሊጥ፣ ዳጉሳና ቆጮ የመሳሰሉት አዝርእት ይጠቀሙ እንደነበር አንዳንድ ማስረጃዎች ያረጋግጣሉ። እናም ጥንታዊ ኢትዮጵያውያን ለዘመናዊው ግብርና የራሳቸው የሆነ አስተማማኝ መሰረተ ድንጋይ እንደጣሉ ከታሪካቸው በቀላሉ መረዳት ይቻላል።
ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ አገሪቱ የራሷ የሆነ የቀን መቁጠሪያ ቀመር (ካለንደር)ና ፊደል ያላት ብቸኛ አፍሪካዊት ሀገር መሆንዋ ተደጋግሞ የተነገረና መላው ዓለም በግልፅ የተገነዘበው ሃቅ ነው። በመሆኑም ኢትዮጵያያን ከጥንት ጊዜ ጀምረን ታሪካችንና ስልጣኔችን የምንገልፅበት ሀገር በቀል የፊደል ገበታና የጊዜ መለኪያ ቀመር ባለቤቶች ነንና እንዚህ የስልጣኔ በሮች ካሉን በርካታ ታሪካዊ እሴቶች ጥቅቶቹ ናቸውና ሊንኮራባቸውና ሊንንከባከባቸው የሚገባን የሀገራችን መገለጫዎች ናቸው።
የጥንት ስልጣኔ አካልና ባለቤትም ነች-ኢትዮጵያ። ከ3000ዓ.ዓ በፊት በምስራቅ አፍሪካ የነበረው የፑንት ስልጣኔ የዛሬይቱ ኢትዮጵያን ያካቲት እንደነበር ይታወቃል።
ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ ከ500 ዓመታት ቅድመ ልደተ ክርስቶስ በፊት ጀምሮ በትግራይ ክልል በአሁኗ አክሱም አካበቢ አንድ አካባቢበዉ በውል የሚታወቅ ‘ድአማት’ የሚባል ግዛት እንደነበር ታሪክ ያስረዳል። ይህም አገሪቱ ከጥንት ጊዜ ጀምሮ ከዘመኑ ጋር የሚሄድ መንግስታዊ መዋቅር እንደነበራትና ከዓረቡ ዓለምም የጠበቀ ግንኙነት መመስረት ችላ እንደነበር የታሪክ ድርሳናት በአንድ ድምፅ ይስማማሉ።
ከድአማት ስልጣኔ በኋላ የተመሰረተውና በወቅቱ ገናና የነበረው የአክሱም ስልጣኔም የጥንታዊ የኢትዮጵያ ታሪክ የማዕዘን ድንጋይ ነው። የአክሱም ስልጣኔ በጣም ገናና በነበረበት ከሁለተኛው እስከ ስድስተኛው ክፍለ ዘመን በርካታ አካባቢዎች የግዛቱ አካል ነበሩ። ለምሳሌ ያህል የዛሬዋ ኤርትራ፣ አብዛኛው ሰሜን ኢትዮጵያ፣ የመን፣ ሳዑዲ ዓረቢያና ሰሜን ሱዳን በዋናነት ተጠቃሾች ናቸው። በተጠቀሰው ጊዜ አክሱም በዓለማችን ከነበሩ አራት ሃያላን መንግስታት አንዷ ነበረች-አክሱም፣ቻይና፣ፐርሺያና ሮማ።
የአክሱም ስልጣኔ በርካታ ያልተነገሩ ታሪካዊ እሴቶችና ቅሪቶች ጥሎ እንዳለፈ ከአንድ ወጥ አለት የተፈለፈሉት የአክሱም ሐወልቶች፣ ክርስቲና እና ኢስላም ሃይማኖቶችና በመሃከላቸው ያለው የመቻቻልና የመከባበር ልምድ የመሳሰሉት ህያው አብነቶች በማየት ብቻ በቀላሉ መግባባት ይቻላል። ኢትዮጵያውያን የምንታወቀው የጥንት ስልጣኔ ባለቤቶችና የጥንታዊ ስልጣኔ አንድ ኣካል በመሆናችን ብቻ ሳይሆን እነዚህ የጥንት ስልጣኔ መገለጫዎቻችን የሆኑ እስቶች በአግባቡ ጠብቀን ከትውልድ ወደ ትውልድ ማስተላለፍ መቻላችን ጭምር ነው። እናም ታሪክና ኢትዮጵያ እንዲሁም ኢትዮጵያና ታሪክ ከማንም ህዝብ በላይ ደግመው ደጋግመው የሚተዋወቁ አካላት ከመሆናቸው በተጨማሪ የጠበቀ ግንኙነትና ትውውቅ አላቸው ቢባልም ስህተት የለውም። ታሪክ ሰሪዎቹ እና የደማቅ ታሪኩ ባለቤቶች ደግሞ እኛ ኢትዮጵያውያን።
የአክሱም ስልጣኔ በተለያዩ ውጫዊና ውስጣዊ ምክንያቶች ሲዳከምና በመጨረሻ ከጨዋታ ውጭ ሲሆንም የአክሱም ስልጣኔ ወደቀ እንጂ የኢትዮጵያ ስልጣኔ ከትውልድ ወደ ትውልድ እንዲሁም ከአንድ አካባቢ ወደ ሌላኛው አካባቢ እየተዘዋወረ መቀጠሉን አላቋረጠም። እናም ላሊበላ፣ ጎንደር፣ሽዋ ፣ሐረር፣ጂማ ወዘተ እያለ ጉዞውን ቀጠለ። እርግጥ ነው አንዴ በጣም ገናና ሲሆን ሌላ ጊዜ ደግሞ የሚቀዛቀዝበት ታሪካዊ ሂደት እንደነበር የታሪክ ድርስናቱ ያወሳሉ።
በማንኛውም ጊዜ ለውጭ ወራሪ ሃይሎች ያልተንበረከከችና በዓለም ዙሪያ ይካሄዱ በነበሩት የ19ኛው ምዕተ ዓመት የነፃነት ትግሎችንም የበኩሏን ድጋፍ ስታደርግ የነበረችና በሁሉም የነፃነት ታጋዮች ስነ-ልቦና ውስጥ አንፀባራቂ ስፍራ የነበራትና ያላት ሀገርም ናት ሀገራችን። የነጮች የበላይነት በገነነበትና እንደ አማልክት በሚታዩበት የ19ኛው ክፍለ ዘመንም ቢሆን ኢትዮጵያ በተደጋጋሚ ይቃጣባት ለነበረው የኢምሪያልስቶች ወረራ ደግማ ደጋግማ እያሳፈረች መልሳቸዋለች። ለዚህም በርካታ የአፍሪካ፣ የላቲን አሜሪካና የካርቢያን ሀገሮች የኢትዮጵያ ሰንደቅዓላ የነፃነት ተምሳሌት አድርገው ስለ ወሰዱት የተወሰነ የአቀማመጥ ማስተካካያና ለውጥ ብቻ በማድረግ የየአገሮቻቸው ባንዴራ አድርገው ተጠቅመውበታል፤ እየተጠቀሙበትም ነው። እናም ያለፈው ትውልድ በወራሪ ሃይሎች ላይ ያስመዘገበው ወርቃማ ገድል እስከ ወዲያኛው ጫፍ ድረስ እየተወሳ ይኖራል። መወሳት ያለበት ድንቅ ታሪክ ነውና።
የውጭ ወራሪ ሃይሎች በሚገርምና በሚያስደንቅ ገድል ካንበረከኩና አሳፍሮ ካሰናበቱ በኋላም በአገሪቱ ለዘመናት ስር ሰዶ የነበረው የአፈናና የግፍ አገዛዝ ኢትዮጵያውያን እጅና እግሮቻቸው አጣጥፈው አሜን ብለው ለመገዛት አልወሰኑም። ስርዓቶቹ ሲፈልጉ ከሰማየሰማያት በመለኰታዊ ሃይል ተመርጠው የተላኩ እንደሆኑ አስመስለው ቢሰብኩ ሌላ ጊዜ ደግሞ በያዙት ምህረት የለሽ አፈሙዝ እየደበደቡ ህዝቡን ለማንበርከክ ቢሞክሩ የኢትዮጵያውያን የአልበገር ባይነት ወኔና መንፈስ ግን ለአፍታም ቢሆን መቆጣጠር አልቻሉም። የኢትዮጵያውያን ስነ-ልቦና ለእኩልነት፣ ለአንድነትና ለፍትሕ ከመቆም ባሻገር ለግፍና ለጭቆና ቦታ አልነበረውምና።
እናም አንዴ በሰሜን ሌላ ጊዜ ደግሞ በደቡብ እንዲሁም በምስራቅና በምዕራብ የተለኰሱ የፍትሕ ችቦዎች ከብዙ ውጣውረድ በኋላ ተጨባጭ ፍሬ አፍርተው ግንቦት 20 ቀን 1983ዓ.ም በሀገሪቱ የነበረው አምባገነናዊ ስርዓት በተባበረው የኢትዮጵያውያን ክንድ ላንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ላይመለስ ተገረሰሰ። በሀገሪቱም አዲስ የእኩልነት፣ የፍትሕ፣ የመከባበርና የመቻቻል ምዕራፍ ተከፍቶ ሁሉም የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በታሪካቸው ለመጀመሪያ ጊዜ ተፈቃቅደውና ተቻችለው የሚኖሩባት ፌዴራላዊ ዴሜክራሲያዊ ኢትዮጵያን እውን አደረጉ። የኢትዮጵያውያን የማያቋሪጥ ታሪክ ሰርነትም በፈላጭቆራጭ ስርዓት መካነ-መቃብር ውስጥ በተከሉት የዴሞክራሲ ችግኝ ዳግም ተበሰረ።
ሀገሪቱ ለበርካታ መቶ ዓመታት አላላውስ ብሎ ቆፍድዶ ይዟት ከነበረው አሃዳዊ አምባገነናዊ ስርዓት ተላቃ በፌዴራላዊ ዴሞከራሲያዊ ስርዓት መጓዝ ከጀመረችም እንሆ 20 ዓመታትን(የሽግግር ጊዜን ጨምሮ) አስቆጥራለች። በእነዚህ 20 ዓመታትም በርካታ የኢኮኖሚ፣የፖለቲካና የማሕበራዊ ልማት እንዲሁም የልማት፣ የዴሞክራሲና የሰላም ስኬቶችና ታሪች ተመዝበዋል።
ባለፉት 20 ዓመታት ከተመዘገቡ ስኬቶች መካከል የሕገ-መንግስቱ መፅደቅና ሕገ-መንግስታዊ ስርዓቱን ተከተሎ በፖለቲካው መስክ የተመዘገበ ድል በግንባር ቀደምትነት የሚጠቀስ ነው። በዚህ ዘርፍ ጎልተው ከሚታዩ የሕገ-መንግስቱ ትሩፋቶች ዋናዋናዎቹን ለመጥቀስ ያህል የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች የሉአላዊ ስልጣን ባለቤቶች መሆናቸወንና ሕገ-መንስግስቱንም የሉኣላዊነታቸው መገለጫ መሆኑን፤ ሕገ-መንግስቱ የሀገሪቱ የበላይ ሕግ ከመሆኑ በተጨማሪ በሕገ-መንግስቱ ከተደነገገው ስርዓት ውጭ የመንግስት ስልጣን መያዝ ሕገ-ወጥ ማድረጉን፤ የዜጎችና የህዝቦች ሰብአዊና ዴሞከራሲያዊ መብቶች ሕገ-መንግስታዊ ዋስትና ማግኘታቸው፣ መንግስትና ሃይማኖት መለያየታቸውና አንዱ በሌላው ላይ ጣልቃ መግባት መከልከሉን እንዲሁም የመንግስት አሰራር ለህዝብ ግልፅ በሆነ መንገድ እንዲከናወን የመንግስት ሕገ-መንግስታዊ ግዴታ አድርጎ በግልፅ ማስቀመጡን ከብዙ ጥቅቶች ናቸው።
አገሪቱና ዜጎቿ በዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ በኩል ካስመዘገቧቸው መሰረታዊ ድሎችና እመርታዎች መካከል ሁሉም ሰዎች በዘር፣ በብሔር፣ በብሔረብ፣ በቀለም፣ በፆታ፣ በቋንቋ፣ በሃይማኖት፣ በፖለቲካ፣ በማሕበራዊ አመጣጥ፣ በሃብት፣ በትውልድ ቦታ፣ ወይም ማንኛውም ዓይነት ልዩነት ሳይደረግባቸው በሕግ ፊት እኩል መሆናቸውና እኩል የሕግ ጥበቃ የሚደረግላቸው መሆኑን፤ የዜጎች የሃይማኖት፣ የእምነትና የአመለካከት ነፃነት ሕገ-መንግስትዊ ዋስትና ማግኘቱን፤የዜጎች የአመለካከትና ሐሳብን በነፃ የመያዝና የመግለፅ መብታቸው የተከበረ መሆነኑን፤ የዜጎች የመደራጀት መብት የሕግ ከለላ ማግኘቱን፤የዜጎች የመምረጥና የመመረጥ መብት መከበሩን፤ እንዲሁም ማንኛውም የኢትዮጵያ ብሔር፣ ብሔረሰብ፣ህዝብ የራሱን ዕድል በራሱ የመወሰን እስከመገንጠል መብቱ በማንኛውም መልኩ ያለገደብ መጠበቁን የአዲስቷ ኢትዮጵያ አዳዲሰ እውነታዎች ናቸው።
በኢኮኖሚው ዘርፍም አገሪቱ አስደናቂና መላው ዓለም የመሰከረለት ስኬት ለማስመዝገብ ችላለች። አገሪቱ ባለፉት ስምንት ተከታታይ ዓመታት ፈጣንና ቀጣይነት ያለው እንዲሁም ምልአተ-ህዝቡን ከፈጣን ዕድገቱ ተጠቃሚ ያደረገ ባለ ሁለት አሃዝ ኢኮኖሚ በማስመዝገብ በዓለማችን ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት ከሚያዝመዝግቡ አገሮች ተርታ ለመሰለፍ ችላለች። በዚህም አገሪቱ በዓለም አቀፍ መድረክ የነበረው የድህነትና የኋላቀርነት ቅጢያዋ ቀስበቀስ እያራገፈች የፈጣንና ቀጣይነት ያለው ዕድገት መገለጫ እየሆነት በዓለም አቀፍ መድረኮች በምሳሌነት ተጠቃሽ ለመሆን በቅታለች።
ኢትዮጵያ በሰብአዊ ልማት ዘርፍም አመርቂ ውጤት እያስመዘገበች እንዳለች መለው ዓለም የሚገነዘበው እውነታ እየሆነ መጥቷል። የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የልማት ፕሮግራም ጥቅምት 25 ቀን 2003ዓ.ም ባወጣው ጋዜጣዊ መግለጫ እንዳስታወቀው ኢትዮጵያ በዓመቱ ውስጥ በሪፖርቱ ከተካተቱ 135 አገሮች የተሻለ አፈፃፀም ነበራት፤በወቅቱ የ2ኛ ደረጃ እንደያዘችም መግለጫው ይመሰክራል።
የሰብአዊ ልማት ከሚረጋገጥባቸው የልማት ዘርፎች አንዱና ዋናው ትምህርት ነው። በመሆኑም አገሪቱ ለትምህርቱ ዘርፍ ልዩ ትኩረት ሰጥታ በመስራቷ በዘርፉ አመርቂ ውጤት እያስመዘገበች ትገኛለች። የአምስት ዓመቱ የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ላይ በግልፅ እንደተቀመጠው በ1997ዓ.ም 16513 የነበረው የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ቁጥር በ2002ዓ.ም ወደ 25217 ከፍ ሲል የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ቁጥርም በተመሳሳይ በ1997ዓ.ም ከነበረው 706 በ2002ዓ.ም ወደ 1202 አድጓል። ከከፍተኛ ትምህርት መስፋፋት አንፃር ደግሞ ከ10 ዓመታት በፊት ከሁለት ያልበለጡ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የነበሩበት አገር በአሁኑ ወቅት በከፍል ወደ ስራ የገቡትን ጨምሮ 22 የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተገንብተው ወደ ስራ የገቡበት ሁኔታ ተፈጥራል። እነዚህ የትምህርት ተቋማት የግል ሴክተሩን አያካትትም። በትምህርት ዘርፍ የተገኘው ስኬት የቁጥር መስፋፋት ብቻ ሳይሆን ስርጭቱንም ቢሆን በፍትሐዊ መንገድ የተከናወነ ነው።
ኢትዮጵያ በጤናው መስክ ባስመዘገበችው አመርቂ ውጤትም በአለም አቀፍ መድረኮች ሳይቀር የመልካም ተሞክሮ ተምሳሌት አገር ሆና ይህንን የስኬት ተሞክሯ ለመላው ዓለም እያካፈለች ትገኛለች። በአሁኑ ወቅት የስኬታማ ፖሊሷ ውጤት የሆኑ 38319 ሴት የጤና ኤክስቴንሽን ሠራተኞች በሁሉም የሀገሪቱ ቀበሌዎች ተሰማርተው ህዝቡን እየረዱ ይገኛሉ። የጤና ተቋማት ግንባታና ሽፋን በተመለከተም በ1997ዓ.ም 4211 የነበረው የጤና ኬላ በ2002ዓ.ም ወደ 14416 ከፍ ሲል የጤና ጣቢያዎች ብዛት ደግሞ በ1998ዓ.ም ከነበረው 644 በ2002ዓ.ም ወደ 1787 አድጋል። የህዝብ ሆስፒታሎች ቁጥርም በተመሳሳይ ሁኔታ በ1998ዓ.ም ከነበረው 79 በ2002ዓ.ም ወደ 111 አሻቅቧል።
በመሰረተ-ልማት ዝርጋታም አገሪቱ መሰረታዊ እመርታ እያሳየች ነው። አገሪቱ በ1983ዓ.ም የነበራት 19ሺህ17 ኪሎ ሜትር መንገድ በ2002ዓ.ም ከ11000 ኪሎ ሜትር በላይ መንገዶች ወደ ኔትዎርኩ በማስገባት አጠቃላይ የሀገሪቱ የመንገድ ርዝመት 49ሺህ ኪሎ ሜትር ደርሷል። በተመሳሳይ ሁኔታ በ1998ዓ.ም ከግማሽ ሚልዮን በታች የነበረው የሞባይል ዝርጋታ በ2002ዓ.ም ወደ 25 ሚልየን አድጓል። በመሆኑም አርሶና አርብቶ አደሩ በተዘረጋለት መንገድና የመረጃ ቴክኖሎጂ በመጠቀም ምርቱን በቀላሉ ከገበያ ጋ ለማገናኘት ችሏል። እናም ሀገሪቱ ህዳሴዋ እውን ለማድረግ ዜጎቿ በአዲሰ መንፈስ እጅለእጅ ተያይዘው የልማቱን አጀንዳ አዲሱ የህወታቸው ዘይቤ አድርገው ለልማትና ዕድገት በጋራ የልማት ሳንባ መተንፈስ ከጀመሩት ሰነባብተዋል።
ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን አሁን ደግሞ ሌላ ታሪክ ለመሰራት ቆርጠው ተነስተዋል። ኢትዮጵያና ታሪክ በደንብ ይተዋወቃሉና አሁንም አዲስ ታሪክ በምድረ ኢትዮጵያ እየተበሰረ ነው። ታላቅ ታሪክ የመስራት ልምድ ያለው ኢትዮጵያዊም በተለመደው አንድነቱና ወኔው የፀረ-ድህነት ትግሉ በማቀጣጠል ከባላንጣው ድህነት ጋር ላንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለመፋታት በታላቁ የህዳሴ ግድብ ስም ቃል ገብቷል። ታሪክ መስራት ካልቀረ ደማቅ ታሪክ መስራት ይበጃልና የአሁኑ ትውልድ ኣባቶቹና ኣያቶቹ በሰሩት ታሪክና ገድል መኩራራት በራሱ በቂ ስላልሆነ የራሱና የኔ የሚለው አስደናቂ የታሪክ አሻራ ለማኖር በሙሉ ልብ ሆ ብሎ ተነስቷል።
ሁሉም ኢትዮጵያውያን ከሰሜን እስከ ደቡብ እንዲሁም ከምስራቅ እስከ ምዕራብ በሁሉም አቅጣጫዎች በአንድ ድምፅ ለአንድ ድምፅ ከማንኛውም ጊዜ በላይ በአንድ ትልቅ የጋራ ጉዳይ ተሳስረው በጋራ እየዘመሩ ነው። አባይን ገዲበው ድህነት ሊሸኙ!
ታላቁ የህዳሴ ግድብ ከመሰረታዊ የኤፌዴሪ መንግስት ልማታዊ ባህሪ የተጠነሰሰና በእድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅዱ የተበሰረ የኢትዮጵያውያን ታሪክ ሰሪነት ደጋግሞ ያረጋገጠ፣ የአንድነታቻን ሁነኛ ማሕተም ሆኖ በአንድ ልብ ያስተሳሰረን የህዳሴአችን ፍኖት ነው። ህዝብና መንግስት በልማት አጀንዳ ዙሪያ የአንድ ሳንቲም ሁለት ገፅታ ብቻ ሳይሆኑ የአንድ ሳንቲም አንድ ገፅታ መሆናቸው ያስመሰከረ የታላቅነታችን ምስጥር ሆኗል ታላቁ ግድባችን።
ታላቁ ግድብ ለመስራት የተነሳሳው ህዝብ ከግድቡ ግንባታ ባሻገር አንድ የማያወላውል ግልፅ መልእክት አለው። የኢትዮጵያ ህዝብ በድህንት ላይ የጀመረው እልህ አስጨራሽ ትግል በሆነና ባልሆነ የመንደር ወሬ እንደማይቀለበስና የውጭ ድጋፍ ቢገኝም ባይገኝም በራሱ ጥረት ታላቅ ታሪክ መስራት እንደሚችል፤ ለዚህም በመካከሉ ያለው የመተማመንና የአንደነት አቅምና እሴት ወሳኝ እንደሆነ የሚያስረዳ የታላቅነት መልእክት። እናም የታሪክ ሰሪዎቿ ሀገር አሁንም የተላላቅ ታሪኮች ማዕከል ሆና ትቀጥላለች። የማያቃሪጥ ታሪክ ተሚሰራባት ሀገር ናትና-ኢትዮጵያ!!
ታላቅ ነበርን ታላቅ እንሆናለን!!