ከፋኖወዲ ሰመራ
Comment on fanowedy@gmail.com
የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ አንድነት መድረክ መጋቢት 17 ቀን 2005 ዓ.ም “የኢትዮጵያን ወቅታዊና መሰረታዊ ችግሮች የመፍቻ አቅጣጫዎች ማኒፌስቶ”
የሚል አንድ ባለ 12 ገፅ ፅሑፍ አስነብቦናል፡፡የዚህ ፅሑፍ ዓላማም መድረክ የሀገሪቱ መሰረታዊ ችግሮች ብሎ በዝርዝር
ላስቀመጣቸው ነጥቦች ለመቃወም አሊያም ለመደገፍ ሳይሆን የኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ በዝርዝር በማስቀመጥ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ
ኢትዮጵያውን የሀገሪቱ ተጨባጭ እውነታ እንዲገነዘቡ እውነተኛ መረጃ ለመስጠት ብቻ ነው፡፡ አንባቢዎች አንድ ነገር ልብ
እንድትሉልኝ እፈልጋለሁ-ይህ ፅሑፍ ሳዘጋጅ የማንኛውም የፖለቲካ ፓርቲ አቋም የመደገፍ አሊያም የመቃወም ፍላጎትም ሆነ ዓላማ
የለኝም፡፡
የመድረክ
“ማኒፌስቶ” አጠቃላይ የዘትና አልፋና ኦሜጋው በኢትዮጵያ ያለው የፖለቲካ ምህዳር ጠቧል የሚል ነው፡፡ የፖለቲካ ምህዳሩ ጠቧል
ወይ ደግሞ ሰፍቷል ከማለታችን በፊት የፖለቲካ ምህዳር ምን ማለት ነው? የፖለቲካ ምህዳር የምጠበው አሊያም ደግሞ የሚሰፋው ምን
ቅድሜሁኔታዎች ሲሟሉ ወይደግሞ ሳይሟሉ ሲቀሩ ነው? የሚሉ ጥያቄዎች አንስቶ መመለሱ በጉዳዩ የተሻለ ግንዛቤ ለመያዝ ጠቃሚ
ይሆናል፡፡
ጄርገን
ሃበርማስ የተባለ ጀርመናዊ የማሕበራዊ ሳይንስ ምሁር እንዳስቀመጠው የፖለቲካ ምህዳር ማለት ዜጎች በአካባቢያቸው በሚከናወኑ
ፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ ምክምያታዊ በሆነ አኳኃን ለመሳተፍ የሚያስችላቸው ዕድል ማለት ነው፡፡ ጥቅል በሆነ አገላለፅ የፖለቲካ
ምህዳር ማለት የአንድ ሀገር ዜጎች በሀገራቸው ጉዳይ ላይ ብንቃት ለመሳተፍ የሚያስችላቸው የተመቻቸ ፖለቲካዊ ሁኔታ መኖር ማለት ነው፡፡ የዜጎች ተሳትፎ ከሚረጋገጥባቸው መሰረታዊ የመጫወቻ
ሜዳዎች መካከል የሕግ የበላይነት ማረጋገጥ፣ በቀጥታ ወይ ደግሞ በተዘዋዋሪ መንገድ በተወካዮቻቸው አማካኝነት ሐሳቦቻቸው
በአግባቡ ለማቅረብ የሚያስችላቸው ሁኔታ መኖር፣ በሚዲያ በኩል ሐሳባቸውና አመለካከታቸው በነፃነት መግለፅ የሚያስችላቸው ሕገ
መንግስታዊ ዋስትና መኖር እንዲሁም የዜጎች የመደራጀት መብት ማረጋገጥ ግንባር ቀደም ተጠቃሾች ናቸው፡፡ የፖለቲካ ምህዳሩ ጠበበ
ወይደግሞ ሰፋ ለማለት እንግዲህ እነዚህ የምህዳሩ መለኪያዎች ፈታ አድርገን እንያቸው፡፡
የኢትዮጵያ
ብሔሮች፣ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የረዥም ጊዜ እልህ አስጨራሽ ትግል ውጤት የሆነው የኢፌዴሪ ሕገ መንግስት በግልፅ እንዳስቀመጠው
ሕገ መንግስቱ የሀገሪቱ የበላይ ሕግ ነው፡፡ ማንኛውም ሕግ፣ ልማዳዊ አሰራር እንዲሁም የመንግስት አካል ወይም ባለስልጣን ውሳኔ
ከዚህ ሕገ መንግስት ጋር የሚቃረን ከሆነ ተፈፃምነት እንደማይኖረው ይደነግጋል፡፡ ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ ማንኛውም ዜጋ፣
የመንግስት አካላት፣የፖለቲካ ድርጅቶች፣ ሌሎች ማሕበራት እንዲሁም ባለስልጣኖቻቸው ሕገ መንግስቱን የማስከበርና ለሕገ መንግሰቱ
ተገዥ የመሆን ግዴታ ጥሎባቸዋል፡፡ ከተግባር እንዳየነውም በመንግስት መዋቅር ከፍተኛ ስልጣን የነበራቸው ጥቅት ግለሰዎች በሕግ
የተሰጣቸው ኃላፊነት ወደ ጎን በመተውና ሕዝቡ የጣለባቸውን አደራ ችላ በማለት ስልጣናቸው አለአግባብ ተጠቅመዋል በሚል
ከስልጣናቸው ሲወርዱ አይተናል፡፡ ለነገሩ ከእነዚህ ጥቅት ግለ ሰዎች መካከል አንዳንዶቹ አሁን የሕግ የበላይነት የለም እያለ
መግለጫ የሚሰጠው መድረክ አቋቁመው ሌላ አማራጭ አፈላልገው በፓርቲ ተረዳጅተው እየተንቀሳቀሱ ነው፡፡ የሕግ የበላይነት
ለማረጋገጥ የሚደረገው ጥረት አነስተኛ ቢሆንማ ኖሮ በአንድ ወቅት የመንግስት ከፍተኛ ባለስልጣናት የነበሩትና በአሁኑ ወቅት
ደግሞ የመድረክ አመራች ሆነው በፓርቲ ተደራጅተው እየተንቀሳቀሰሱ ያሉ አንዳንድ ግለሰዎች ከመንግስት ስልጣናቸው ባልወረዱ
ነበር፡፡
የሃይማኖት፣የእምነትና
የአመለካከት ነፃነትም በሀገሪቱ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ሕገ መንግስታዊ ዋስትና አግኝተዋል፡፡ ይህ ደግሞ ሁሉም ኢትዮጵያዊ
የሚገነዘበው የአደባባይ ምስጥር ነው፡፡ ማንኛውም ሰው የመረጠውን ሃይማኖት ወይም እምነት የመያዝ ወይም የመቀበል፣ሃይማቱንና
እምነቱን ለብቻ ወይም ከሌች ጋር በመሆን በይፋ ወይም በግል የማምለክ፣የመከተል፣የመተግበር፣ የማስተማር ወይም የመግለፅ መብቱ
ሕገ መንግስታዊ ዋስትና አግኝቷል፡፡ የሕገ መንግስቱ መርሆዎች ምን ያህል ተግባራዊ እየሆኑ እንዳሉ በቀላሉ ለመረዳት በአዲስ
አበባ ያለው አንድ ማሳያ ብቻ በማቅረብ ጉዳዩ የበለጠ ግልፅ ለማድረግ እሞክራለሁ፡፡ የእስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት
የካቲት 22 ቀን 2005ዓ.ም ከሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ መረዳት እንደምቻለው ከ23 ዓመት በፊት በከተማው 12 መስጊዶች ብቻ
የነበሩ ሲሆን ሕገ መንግሥቱ ባረጋገጠው የእምነትና የሃይማት ነፃነት መሰረት በአሁኑ ስዓት ከ220 በላይ መስጊዶች አገልግሎት
በመስጠት ላይ ይገኛሉ፡፡ እናም መድረክ የሃይማት እኩልነትና ነፃነት አስመልክቶ ያቀረበው ሐሳብ ከትዝብት የበለጠ ዋጋ ያወጣል
የሚል እምነት የለኝም፡፡
የፖለቲካ
ምህዳሩ መስፋት ወይም መጥበብ ከሚለካባቸው መስፈርቶ ሌላኛው ደግሞ የመደራጀት መብት ነው ብለናል፡፡በኢፌዴሪ ሕገ መንግስት
አንቀፅ 31 በግልፅ እንደሰፈረው ማንኛውም ሰው አግባብ ያለው ሕግ በመጣስ ወይም ሕገ መንግስታዊ ስርዓቱ በሕገ ወጥ መንገድ
ለማፍረስ እስካልተንቀሳቀሰ ድረስ ለማንኛውም ዓላማ በማሕበር የመደራጀት መብቱ ሕገ መንግስታዊ ዋስትና አግኝቷል፡፡
የዜጎች
የመደራጀት መብት ከሚረጋገጥባቸው ሁነኛ አደረጃጀቶች መካከል የፖለቲኪካ ፓርቲዎች ተጠቃሾች ናቸው፡፡ የኢፌዴሪ የፖለቲካ
ፓርቲዎች የምዝገባ አዋጅ ቁጥር 573/2000 አንቀፅ 4/1 ላይ እንደተቀመጠው ማንኛውም ኢትዮጵያዊ የፖለቲካ ፓርቲ የማቋቋም
ወይም የፖለቲካ ፓርቲ አባል የመሆን መብት እንዳለው ተደንግጓል፡፡ የፖለቲካ ፓርቲ የማቋቋም ወይ ደግሞ በማንኛውም ሕጋዊ
የፖለቲካ ፓርቲ አባል ሆኖ የመሳተፍ መብት ብቻም ሳይሆን የፓርቲዎች ህልውና ለማረጋገጥ ሲባልም ፓርቲዎቹ ከመንግስት የፋይናንስ
ድጋፍ የሚያገኙበት ሕጋዊ ማዕቀፍ ተዘጋጅቶ ተግባራዊ እየሆነ ነው፡፡ ከመንግስት ለፓርቲዎች የሚሰጠው ድጋፍም በክልል ወይም
በፌዴራል ደረጃ ባላቸው የመቀመጫ ብዛት እንደሆነ ይደነግጋል፡፡ ይህ ማለት ደግሞ የሚመደበው ገንዘብ የዜጎች ይሁንታ ላገኙ
ፓርቲዎች ነው ማለት ነው፡፡ ምክንያቱም ፓርቲዎቹ በጀርባቸው የተለያየ ፖለቲካዊ አመለካከት ያለው ዜጋ ስለተሰለፈ ነው፡፡ ይህ
እንደተጠበቀ ሆኖ ፓርቲዎቹ በምርጫ ወቅት ባቀረቡት የዕጩ ብዛትና በሚያቀርቡት የሴት ዕጩዎች ብዛት መሰረት እንደሆነም በአዋጁ
አንቀፅ 45 ንኡስ አንቀፅ 2 እና 3 በግልፅ የሰፈረ ነው፡፡ እናም ፓርቲዎቹ ባላቸው የመቀመጫ ብዛት ብቻ ሳይሆን ምንም
ዓይነት የምክር ቤት መቀመጫ እንኳን ባይኖራቸው በሚያቀርቡት ዕጩ ተወዳደሪ ብዛት በተለይ ደግሞ ባላቸው የሴት ዕጩዎች ብዛት
የመንግስት የፋይናንስ ድጋፍ በማግኘት የፖለቲካ ስራቸውን ማከናውን የሚያስችላቸው ዕድል ያገኛሉ ማለት ነው፡፡
አሁንም
የፖለቲካ ምህዳሩ መጥበብ ወይም መስፋት ከማውራታችን በፊት በሀገሪቱ የተመዘገቡ የፖለቲካ ፓርቲዎች ብዛት ደግሞ እንመልከት፡፡
የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ መረጃ እንደሚያመላክተው በምርጫ 2005ዓ.ም የሚሳተፉ 79 ፓርቲዎች ተመዝግበዋል፡፡ ዘጠኝ ክልሎችና
ሁለት የከተማ መስተዳድተሮች እንዲሁም 80 የሚሆኑ ብሔሮችና ብሔረሰቦች ባሉባት ኢትዮጵያ 79 የፖለቲካ ፓርቲዎች ተመዝግበው
ለምርጫ ይወዳደራሉ ሲባል የቱ ላይ ነው የፖለቲካ ምህዳሩ ጠበበ የሚያስብል ቁምነገር የተገኘው! ይህ እንዳለ ሆኖ 30642608
ዜጎች በመራጭነት እንደተመዘገቡም ቦርዱ ይፋ ያደረገው መረጃ ያስረዳል፡፡ እናም የመድረክ የፖለቲካ ምህዳር መጥበብ ከዚህኛው
መስፈርት አንፃር ሲመዘን “የማኒፌስቶው” የቀለም ዋጋ እንኳን መመለስ የሚያስችለው አይመስለኝም፡፡
ዜጎች
ሐሳባቸውን በነፃነት መግለፅ የሚያስችላቸው ሚዲያ መኖርና አለመኖርም የፖለቲካ ምህዳሩ መጥበብና መስፋት ለመለካት ሌላው መለኪያ
ተደርጎ ይወሰዳል፡፡ የኢፌዴሪ ሕገ መንግስት አንቀፅ 29 ላይ እንደተደነገገው ማንኛውም ሰው ያለ ማንም ጣልቃ ገብነት ሓሳቡን
የመግለፅ ነፃነት አለው፡፡ ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ በተለይ የፕሬስ ነፃነት ለማረጋገጥ ሲባል የቅድሚያ ምርመራ በማንኛውም መልኩ
ከመከልከሉ በተጨማሪ ፕሬስ የህዝብ ጥቅም የሚመለከት መረጃ የማግኘት ሕገ መንግስታዊ መብትም ተጎናፅፏል፡፡
የመገናኛ
ብዙሃንና የመረጃ ነፃነት አዋጅ ቁጥር 590/2000 የሚዲያ ኢንዱስትሪው ከመገንባት አንፃር በኢፌዴሪ መንግሥት ከተወሰዱ
እርምጃዎች ግንባር ቀደም ተጠቃሽ ነው። በአዋጁ የመገናኛ ብዙሃን ነፃነት በሚያብራራው አንቀፅ አራት ንኡስ አንቀፅ ሶስት ላይ
ማንኛውም የመንግስት አካላት መገናኛ ብዙሃን ማሕበራዊ ተግባራቸውን ለመወጣት ሀ) ዜና ወይም መረጃን የመሰብሰብ፣ የመቀበልና
የማሰራጨት፣ ለ) በልዩልዩ ጉዳዮች ላይ አስተያየት ወይም ትችት የማቅረብ ወይም፣ ሐ) የተለያዩ ሌሎች ዘዴዎችን በመጠቀም
የህዝብን አስተያየት በመቅረፅ ሂደት የመሳተፍ መብታቸውን ማክበር እንዳለበት ይደነግጋል።
አሁንም
ቢሆን የፖለቲካ ምህዳሩ ጠበበ አሊያም ሰፋ ከማለታችን በፊት በሕገ መንግስቱና የመገናኛ ብዙሃንና የመረጃ ነፃነት አዋጅ ላይ
የተደነገጉ የፕሬስ ነፃነት መርሆዎች በተግባር ላይ እንዴት እንዳሉ ደግሞ በአጭሩ እንመልከት፡፡ የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ
ባለስልጣን መረጃ እንደሚያመላክተው እስከ ጥር 2005ዓ.ም ባለው ጊዜ ውስጥ 91 መፅሔቶችና 144 ጋዜጦች በድምሩ 144
የሚሆኑ በተለያዩ ቋንቋዎች የሚታተሙ ከአንድ ክልል በላይ ስርጭት ያለቸው የፕሬስ ውጤቶች ከባለስልጣኑ ፈቃድ ወስደዋል፡፡
ከጋዜጦችና መፅሔቶች በተጨማሪም ሕብረተሰቡ በራሱ ቋንቋ ሐሳቡን የሚገልፅባቸው፣ ባህሉንና ታሪኩን የሚያስተዋውቅባቸውና
የሚያቅብባቸው 16 የማሕበረሰብ ሬድዮ ጣቢያዎች ፈቃድ እንደወሰዱ
የባለስልጣኑ መረጃ ያስረዳል፡፡ እነዚህ መረጃዎች በየክልሉና በየአካባቢው እየተሰራጩ ያሉ ጋዜጦችና መፅሔቶች አያካትትም፡፡
ዜጎች ስለ መብታቸው በነፃነት መናገርና መፃፍ ይቅርና “አስበህ ይሆናል” እየተባሉ በሚሰቃዩባትና ያለ ፍርድ ቤት ትእዛዝ
በየመንገዱ በቀይሽብር እያለቁባት በነበረችው ኢትዮጵያ ባለፉት 21 ዓመታት በሚዲያው ዘርፍ የተገኘው ለውጥ በምንም ሒሳብ ይለካ
በምን ውጤቱ አበረታች ነው፡፡
እላይ
ከተጠቀሱ ተጨባጭ እውነታዎች እንደተገነዘብነው የሕግ የበላይነት የተረጋገጠባት፣ የህዝቦች ተሳትፎ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተጠናከረ በመጣባት፣ የሚዲያው ዕድገት በየጊዜው እየተሻሻለ
በሚገኝባት፣ የዜጎች የሐሳብ፣ የአመለካከት፣ የእምነትና የሃይማኖት ነፃነት በሕገ መንግስቱና በተግባር በተረጋገጠባት ኢትዮጵያ
የፖለቲካ ምህዳሩ ጠቧል የሚለው ፈልጥ ውሃ የሚቋጥር ጭብጥ እንደሌለው መደምደም ይቻላል፡፡
መድረኩ
“ማኒፌስቶ” ብሎ ባዘጋጀው ባለ 12 ገፅ ፅሑፍ ካሰፈራቸው ነጥቦች ሌላኛው ደግሞ የኢትዮጵያ መንግስት ከለጋሾች የሚያገኘው
እርዳታ ለፖለቲካ ዓላማ እያዋለው ነው የሚል ነው፡፡ በነገራችን ላይ ይህ አባባል የመድረኩ አባል የሆኑት አቶ ስዬ እብርሃ
በ2002ዓ.ም ባዘጋጁት ፅሑፍ በስፋት ለማብራራት ሞክረው ነበር፡፡ ዓለም አቀፉ የለጋሾች ቡድንም ኢትዮጵያ ከለጋሾች የምታገኘው
ድጋፍ ለፖለቲካ ዓለማ እያዋለችው ነው መባሉ እንዳሳዘነው ገልፆ ጉዳዩ ፍፁም ከእውነት የራቀና ተራ አሉቧልታ እንደሆነ በወቅቱ
ምላሽ የሰጠበት ነው፡፡ በ2002ዓ.ም ብቻም ሳይሆን ቡድኑ በያዝነው ወር መጀመሪያ ባወጣው መግላጫም ኢትዮጵያ ድህነትን
ለመቀነስ እያደረገች ያለችው ጥረት አድናቆት እንደሚቸረው የቡድኑ ተባባሪ ሊቀመንበር ምስክርነታቸው ሰጥተዋል። እንደ ተባባሪ
ሊቀመንበሩ አገላለፅ አገሪቱ ከድህነት ለመውጣት የምታደርገው እንቅስቃሴ አበረታች ደረጃ ላይ ይገኛልም ብለዋል። የኢፌዴሪ
መንግሥት አገሪቱን ከድህነት ለማውጣት የሚችል ትክክለኛ ፖለሲዎች ቀርጾ ሥራ ላይ እያዋለ መሆኑንም ሚስተር ጌኡት ለጋዜጠኞች
አስረድተዋል።
ማን
ይናገር የነበረ ማን ያርዳ የቀበረ እንዲሉ ለጋሾቹ የኢትዮጵያ መንግስት ትክክለኛ ፖሊሲ ቀርፆ ሀገሪቱ ወደ ተሻለ የዕድገት
ደረጃ ለማሸጋገር በቁርጠኝነት እየሰራ ነው፡፡ ከለጋሾች የሚያገኘው ድጋፍም በትክክል ለድህነት ቅነሳ ስራው እያዋለው ነው ብለው
በሚመሰክሩበት አኳኃን የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ አንድነት መድረክ ደግሞ ይህን በባለቤቱ በኩል ስህተት መሆኑ በተደጋሚ የተነገረለት
ጉዳይ ምርጫ በመጣ ቁጥር እያሳደሰ በአጀንዳነት ያቀርበዋል፡፡
ሌላው
የሚገርመው ነገር ፓርቲው በአንድ በኩል ህዝብን በመወከል እንቀሳቀሳለሁ ብሎ ሲናገር እዛው ሳለ ደግሞ “ማኒፌስቶው” የወጣቶችና
የሴቶች ማሕበራት፣ ባለሃብቶችና የተለያዩ የሙያ ማሕበራት ገዥ ፓርቲ በጥቅማጥቅም የሚቆጣጠራቸው እያለ ይኮንናቸዋል፡፡
በሕብረተሰቡ ውስጥ ከግማሽ በላይ የሚሆኑት ሴቶችና አደራጃጀታቸው እየኮነኑ፣ የነገይቲ ኢትዮጵያ
ሀገር ተረካቢ የሆነው ወጣቱን ትውልድና አደረጃጀቱን እየረገሙ፣ በተለያየ የሙያ ዘርፍ ተሰልፈው ሀገራቸው ለመገንባት እየተረባረቡ
ያሉ ሙያተኞችና አደረጃጀታቸው እያጣጣሉ የመድረክ ህዝባዊነትና ዴሜክራሲያዊነት የቱ ላይ እንደሆነ ግልፅ ነው፡፡ በመድረክ
አገላለፅ በሰላማዊ መንገድ ሀገሩን ለመገንባት የተሰለፈ ኃይል በሙሉ ወንጀለኛ ሆኗል፡፡ ይህ የሚለበት ምክንያት “በማኒፌስቶው”
ሰባተኛው ገፅ ላይ “ሀገሪቱን ወደ ጨለማ ዘመን መልሶ በኢትዮጵያ የተቃውሞ መገለጫ ብቸኛው መንገድ በሃይል መጠቀም ነው”
ወደምለው ድምዳሜ እንዳደርስ ስጋት እንዳለው የሚገልፅበት የአመፅ ጥሪ በማስፈሩ ነው፡፡
በሌላም
በኩል መድረኩ በኢትዮጵያ ተመዘገበ ስለሚባለው ኢኮኖሚያዊ እድገት የኢህአዴግ ድስኩር እንደሆነ በስፋት ያትታል፡፡ ባለፉት 21
ዓመታትም በሀገሪቱ የተመዘገበ ዕድገት እንደሌለ ይደመድማል፡፡ ለመሆኑ ኢትዮጵያ ባለፉት ተከታታይ ዘጠኝ ዓመታት ስላስመዘገበችው
ኢኮኖሚያዊ ዕድገት የኢፌዴሪ መንግስትና ዓለም አቀፉ መሕበረሰብ እንዴት ይገልፁታል፡፡
ስለአጣቃላይ
የሀገሪቱ ዕድገት ከማውሳታችን በፊት በየዘርፉ የተመዘገቡ ዕድገቶች ፈታ አድርጎ ማየቱ ጠቃሚ ይሆናል። ከሰብአዊ ልማት
እንጀምር። የሰብአዊ ልማት ከሚረጋገጥባቸው የልማት ዘርፎች አንዱና ዋናው ትምህርት ነው። በመሆኑም አገሪቱ ለትምህርት ልማት
ዘርፍ ልዩ ትኩረት ሰጥታ በመስራቷ በዘርፉ አመርቂ ውጤት እያስመዘገበች ትገኛለች። መንግሥት አገሪቱን ወደ ላቀ የዕድገት ደረጃ
ለማሸጋገር ነድፎ ተግባራዊ እያደረገ ባለው የአምስት ዓመቱ የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ላይ በግልፅ እንደተቀመጠው
በ1997 ዓ.ም 16ሺህ 513 የነበረው የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ቁጥር በ2002 ዓ.ም ወደ 25ሺህ 217 ከፍ ሲል
የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ቁጥርም በተመሳሳይ በ1997 ዓ.ም ከነበረው 706 በ2002ዓ.ም ወደ 1ሺህ 202 አድጓል።
ከፍተኛ
የትምህርት ተቋማትን ከማስፋፋት አንፃር ደግሞ ከአስር ዓመት
በፊት ከሁለት ያልበለጡ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የነበሩበት አገር በአሁኑ ወቅት በከፊል ወደ ስራ የገቡትን ጨምሮ 31
የመንግሥት ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተገንብተው ተግባራዊ እንቅስቃሴ የጀመሩበት ሁኔታ ተፈጥራል። መንግሥት የከፍተኛ ትምህርት
ተቋማትን ተደራሽነት ለማረጋገጥ ትክክለኛ ፖሊሲ ነድፎ ተግባራዊ በማድረጉ በርከታ የግል ባለሃብቶች በዘርፉ ተሰማርተው አበረታች ውጤት
እያስመዘገቡ ይገኛሉ። በትምህርት ዘርፍ የተገኘው ስኬት የቁጥር መስፋፋት ብቻ ሳይሆን ስርጭቱም በፍትሐዊነት
እየተከናወነ ነው።
በጤናው
መስክም ቢሆን መድረክ በ“ማኒፌስቶው” እንደገለፀው በአካባቢያቸው የጤና ተቋሞች ባለመኖራቸው አሊያም የህክምና ተቋማቱ በሃይለኛ
ጫና ላይ በመውደቃቸው እናቶች ለእንግልት ተዳርጓል በሏል፡፡ እውነታው ግን በሀገሪቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገና እየተሻሻለ
በመጣው የመሰረተ ጤና አቅርቦት ሀገሪቱ በአለም አቀፍ መድረኮች ሳይቀር የመልካም ተሞክሮ ተምሳሌት አገር በመሆን ይህንን
የስኬት ተሞክሯ ለመላው ዓለም እያካፈለች ትገኛለች። በአሁኑ ወቅትም ከ38ሺህ በላይ ሴት የጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎች በሁሉም
የሀገሪቱ ቀበሌዎች ተሰማርተው ህዝቡን እያገለገሉ ይገኛሉ። የጤና ተቋማት ግንባታና ሽፋንን በተመለከተም በ1997 ዓ.ም 4ሺህ
211 የነበረው የጤና ኬላ ቁጥር በ2002 ዓ.ም ወደ 14ሺህ 416 ከፍ ሲል የጤና ጣቢያዎች ብዛት ደግሞ በ1998 ዓ.ም
ከነበረው 644 በ2002 ዓ.ም ወደ 1ሺህ 787 አድጓል። የህዝብ ሆስፒታሎች ቁጥርም በተመሳሳይ ሁኔታ በ1998 ዓ.ም
ከነበረው 79 በ2002 ዓ.ም ወደ 111 አሻቅቧል።ይህ አሃዝ በግል ባለሃብቶች የተገነቡ የጤና ተቋማት ግምት ውስጥ
አላስገባም፡፡ እናም የመድረክ መረጃ ከእውነት የተፋታ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡
የመንግሥታቱ
ድርጅት የ2013 የሰብዓዊ ልማት ሪፖርት እንዳስቀመጠው ኢትዮጵያ በሰብዓዊ ልማት ረገድ በዓለም ሦስተኛ በአፍሪካ ደግሞ
ሁለተኛዋ ፈጣን ለውጥ ማሳየት የቻለች አገር ሆናለች፡፡ የድርጅቱ የልማት ፕሮግራም ተወካይ ኡጂን ኦውሱ ሪፖርቱን አዲስ አበባ
ውስጥ ይፋ ባደረጉበት ወቅት እንዳሉት ኢትዮጵያ በሰብዓዊ ልማት ረገድ ፈጣንና ተጨባጭ ለውጥ ማስመዝገብ ከቻሉ ቀዳሚ ሀገራት
ግንባር ቀደም ተጣቃሽ ናት። እንደ ተወካዩ አገላለፅ ኢትዮጵያ እ.አ.አ ከ2000 ጀምሮ ባሉት 13 ዓመታት ውስጥ የሰብዓዊ
ልማት አፈፃጸሟ 44 በመቶ ያህል መሻሻል ማሳየቱን አስታውቀዋል።
በመሰረተ-ልማት
ዝርጋታም አገሪቱ መሰረታዊ የእመርታ ለውጥ እያሳየች ነው። በአገሪቱ የመንገድ ዘርፍ ልማት ፕሮግራም በ1989 ዓ.ም ሲጀመር
ከነበረው 26ሺህ 650 ኪሎ ሜትር መንገድ በ2002 ዓ.ም 48ሺህ 800 ኪሎ ሜትር ደርሷል። በተመሳሳይ ሁኔታ በ1998 ዓ.ም
ከግማሽ ሚሊዮን በታች የነበረው የሞባይል መሥመር ዝርጋታ በ2002 ዓ.ም ወደ 25 ሚሊዮን አድጓል። በመሆኑም አርሶ አደሩ እና
አርብቶ አደሩ በተዘረጋለት መንገድና የመረጃ ቴክኖሎጂ በመጠቀም ምርቱን በቀላሉ ከገበያ ጋር ለማገናኘት ችሏል።
የአፍሪካ
ኢኮኖሚክ አውትሉክ የ2012 ሪፖርት እንዳስቀመጠው እ.አ.አ ከ2004 ጀምሮ ሪፖርቱን እስከተጠናቀቀበት ድረስ በኢትዮጵያ
ፈጣንና ቀጣይነት ያለው ዕድገት ማረጋገጥ ተችሏል፡፡ በሪፖርቱ ላይ በግልጽ እንዳስነበበው በ2013 ቅናሽ የታየ ቢሆንም
የኢትዮጵያ ዕድገት ፈጣን ነበር ብቻም ሳይሆን በሚቀጥሉት ዓማታትም ቢሆን በአፍሪካ ፈጣን ዕድገት ማስመዝገብ የሚትችል አገር
እንደሆነች ከወዲሁ መተንበይ ችሏል፡፡ በአሁኑ ጊዜ ያለው የዋጋ ግሽበትም ቢሆን መድረክ እንዳለው የ42% ወይም 45% ጭማሪ
ሳይሆን በጥር ወር ከነበረው 12.5% በየካቲት ወር ወደ 10.3% እንደወረዳ ነው፡፡ ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅትም (IMF)
የሀገሪቱ የዋጋ ንረት እንደቀነሰ ገልፆ አሁን ያለው ጥብቅ የመኒተሪና የፊዚካል ፖሊሲ ማስቀጠል ከተቻለ በኢትዮጵያ ያለው የዋጋ
ንረት ወደ ነጠላ ድጂት ማውረድ ይቻላል እያለ ነው፡፡ እዚህ ላይ የዋጋ ንረቱ በዘላቂነት ለመቆጣጠርና የተረጋጋ የገበያ ሁኔታ
ለመፍጠር መንግስት አሁንም ቢሆን በበለጠ ተግቶ መስራት እንዳለበት ጥያቄ የለውም፡፡
የመድረክ
“ማኒፌስቶ” በእስካሁኑ ጉዳዮች ብቻ ሳይወሰንም “የፖለቲካ ምህዳሩ ሰፍቶ ለሁሉም ዴሞክራሲያዊ ሃይሎችና ለመላው ህዝባችን
ተደራሽ እንዲሆን ከገዥው ፓርቲ ኢህአዴግ ጋር ለመወያየትና ዝግጅነቱን በድጋሚ ያረጋግጣል”ይላል፡፡ እውነታው ግን ሁሉም
ኢትዮጵያዊ የሚያውቀው ነው፡፡ አብዛኞቹ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎችና ገዥው ፓርቲ የተስማሙበት የፓርቲዎች የስነ ምግባር ደንብ
አልፈርምም ብሎ መድረክ ረግጦ የወጣው መድረክ አሁን ደግሞ ራሱ በራሱ ላጣጣለው ውይይት ተመልሶ ዝግጁነቱን ሲያረጋግጥ ሕግ
ደንግግና ተመልሰህ አፍርሰው (Making Rules and Breaking Rules) ከሚለው የማኪያቬሊዝም ተለዋዋጭና መርህ
አልቦ አካሄድ አንድ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡
የመድረክ
“ማኒፌስቶ” በአጭር አገላለፅ ለማስቀመጥ ያህል በአንድ በኩል የፓርቲው ዓላማና መርህ ከማስቀመጥ ይልቅ በተለመደው የወቀሳና
የማጥላላት ዘመቻ ላይ ያነጣጠረች ከመሆኗ በተጨማሪ ያቀረበቻቸው ጭብጦችም ቢሆኑ በዝርዝር ሲፈተሹ ውሃ የማይቋጥሩ የተለመዱ
ሸፍጦች ናቸው እላለሁ፡፡
No comments:
Post a Comment