በአሜሳይ
ከነዓን
በሀገራችን በሙያቸው፣ በስነምግባራቸውና በሚያንፀባርቋቸው ሚዛናዊና አሳማኝ
ሃሳቦች የበርካታ ሰዎችን ቀልብ የገዙና አንቱታን ያተረፉ ሙያተኞች
በርካቶች ናቸው፡፡ የግል ህይወታቸውን ወደ ጎን በመተው ለዘመናት ያካበቱትን እውቀትና ልምድ በአግባቡ ለሀገራቸው ጥቅም በማዋል
ስለቆሙለት ዓላማ መስዋዕት የሚከፍሉ የህክምና ባለሙያዎች፣ መሃንዲሶች፣ መምህራን፣ የህግ ባለሙያዎች፣ ብቻ በየስራ መስኩ ይበል
የሚያሰኝ ተግባር የሚፈፅሙ የሀገራችን አለኝታዎች ብዙ ናቸው፡፡ በእነዚህ የተከበሩ ሙያተኞች አስተዋፅኦም የሀገራችን ዕድገት እየተፋጠነ፣
ሀገራችንም በዓለማችን ፈጣን ዕድገት ከሚያስመዘግቡ ጥቂት ሀገራት ተርታ እያሰለፋት ይገኛል።
አንዳንዶች ደግሞ እንደው የተለጠፈላቸውን ስም ብቻ እንደ ትልቅ ቁም ነገር
ቆጥረው ንግግራቸው፣ አስተያየታቸውና መላምታቸው እንኳንስ ቀልባችንን ሊገዛን ቀልባችንን ሲገፈን፤ ኡፍ! ደግሞ ጀመረ እስከማለት
ያደርሱናል፡፡ በእያንዳንዱ እንቅስቃሴአቸውም አላዋቂነታቸው ገዝፎ ይታያል። ንግግራቸውን ሆን ብለው በማጣመም፣ የተውገረገሩ ሃሰተኛ
መላምቶች በማስቀመጥ በርካቶችን በሀሰት መረጃ ለማደናበር ቀን ተሌሊት ይኳትናሉ! አለን የሚሉት ሙያቸውን ላልባሌ ነገር ያውም የሙያው
ስነ-ምግባር ለማይፈቅደው ተራ ነገር ሲጠቀሙበት ይስተዋላሉ፡፡ ለዚህ አባባሌ ጥሩ ማሳያ የሚሆነኝ ላለፉት ወራቶች በየጋዜጣና በየመፅሔቱ
የተጣመሙና የተውገረገሩ መረጃዎችንና ከጉዳዩ ጋር ተያያዥነት የሌለው “ትንታኔ” በማቅረብ ከእውነት ጋር እንድንጣላ የሚኳትነው “የሕግ
ባለሙያ” የሚል ቅፅል ስም እየሰጠ የሚወተውተን ተማም አባቡልጉ ነው፡፡
ስለግለሰቡ ጫፍ የወጣ ትንታኔ ብዙ ማለት ቢቻልም ለዛሬ ፅሁፌ ማጠንጠኛ
ማድረግ የፈለግኩት በሎሚ መፅሄትና በኢትዮ ምህዳር ጋዜጣ የፃፋቸውና ተጠይቆ ያላቸውን ሃሳቦች ይሆናል፡፡ የፀረ ሽብርተኝነት ህጉ
የሚከሰው ዲሞክራሲን ነው፣ መንግስታዊ ሽብርተኝነት፣ ልፋ ያለው አንድ እንጨት ያስራል እና ሕገ መንግስታዊውን ስርዓት የናደው የኢትዮጵያ
መንግስት ነው! በሚል ጎላ ደመቅ አድርጎ በተጠቀመባቸው ርዕሶች ውስጥ ባሉ ጭብጥ የሌላቸው ሃተታዎች ላይ ያንፀባረቀው ሃሳብ የሰውዬውን
ዓላማ በግልፅ ለመረዳት ያግዛል፡፡ በእርግጥ እነዚህ ፅሁፎች እርሱ ምሁር መስሎ በመቅረብ ለመተንተን የሞከረበት ግን ደግሞ በጥሞና
ላነበበው ይሄ ሰው ምን ነካው የሚያስብል፤ በስሜት የታጨቀ የወረደ ተራ ፅሑፍ ሆኖ አግኝቼዋለሁ፡፡
በተለይ የፀረ ሽብርተኝነት አዋጁ ጥሩ ዘበኛ እንደሆነ ከአገላለፁ መረዳት
ይቻላል፡፡ የፀረ ሽብርተኝነት አዋጁ ራስ ህመም ይሆንባቸዋል ብዬ የማስባቸው ከጉዳዩ ጋር በቀጥታ አልያም በተዘዋዋሪ ግንኙነት ያላቸው
ሰዎች ናቸውና አቶ ተማም ምን ነካው የሚል ጥያቄ እንዳነሳ አስገድዶኛል? ካልሆነ ደግሞ ጥብቅናው ለሕግና ሕገመንግስታዊ ስርዓቱ
ሳይሆን ለሕገወጥነትና ከሽብር ጋር ግንኙነት ላላቸው አካላት በመሆኑ ህግን እንደፈለገ እያጣመመ በሚያንፀባርቃቸው ወሬዎች አሸባሪዎችና
ተጠረጣሪዎች ሕግ የማይመለከታቸው ለመሆና ቸው ሊያስረዳን ፈልጎ ይሆናል እላለሁ! ድሮውንስ ጠበቃ አይደል!
እንደልባቸው የመሰላቸውን በመዘባረቀ ከሚፈነጩት አንዳንድ የግል የህትመት
ውጤቶች ፊት ገጽ አልያም በውስጥ ገፆቻቸው የፅሁፎቻቸው ማዳመቂያም፤ የህትመት ውጤቶቻቸው ማሻሻጫም አድርገው እየተጠቀሙበት ይመስላል
ጠበቃ ተማም ምንም አለ ምን ብቻ ከአንዱ ገፅ ላይ ጉብር ማለት ወሳኝ ስራው ያደረገው ይመስላል። ለነገሩማ ይህም እኮ ጥብቅና ሊሆን
ይችላል ጎበዝ!
የሕግ ባለሙያ ሕግ ያለአግባብ እንዳይጣስ፣ ሰዎች በህግ ክፍተት ያለአግባብ
ጉዳት እንዳይደርስባቸው ህግና ህጋዊ አሰራርን ብቻ ማዕከል ያደረገ የህግ የበላይነት አክብሮ እንዲከበር የሚንቀሳቀስና ለሕግ የበላይነትም
ከልቡ የሚታገል ሰው ነው። ጠበቃው ተማም የህግ ትምህርቱን የት እንደተከታተለው መረጃው ባይኖረኝም መቼም ከምንም ተነስቶ
የህግ ባለሙያ የሚል የተከበረ ስም እንዳልተሰጠው እገምታለሁ፡፡ ቅሉ ምን ያደርጋል ህግ እያጣመመ ህጉ ከሚፈቅድለት የሙያ ስነምግባር
ውጭ ድንበር በመጣስ የሚዛናዊነት ትርጉም ተዛብቶበት ገሀድ የወጣ የጥላቻ ፖለቲካውን በስመ “የሕግ ባለሙያ” በነተበ ብዕሩ በማራመድ
የሕግ ምሁርነቱን ምንነት በግልፅ የሚያስረዳ ሆነ እንጂ! እናም “ጠበቃ” ተማም ሕግን ሕግ እንደማይገዛት እስኪመሰለን የሕግ ሙያውን
ሕገ ወጥ ተግባራትን ለማደፋፈርና ለማቆለጳጰስ ተጠቀመበት!
በኢትዮ ምህዳር ጋዜጣ ሐምሌ 23 መንግስታዊ ሽብርተኝነት በሚል ርዕስ
ለንባብ ያበቃው ፅሁፍ የስነ-ምግባር ሽፍታውና የ”ሕግ ባለሙያ”ው
ተማም መንግስት በዜጎቹ ላይ መንግስታዊ ሽብርተኛነት ፈፅሟል ሲል ክሱን አሰማን!፡ ጽንሰ ሃሳቡን ሲያብራራ መንግስታዊ ሽብርተኝነት
መንግስት በዜጎች ላይ በሙሉ ወይም በከፊል የሚፈፅመው የግድያ፣ የእስራትና ሌሎች ህገ ወጥ እርምጃዎች እንደሆኑም እንዲሁ በዘፈቀደ
ተረተረው፡፡ ይህ ትንታኔው ታዲያ መቋጫው መንግስት አልሞና አቅዶ በዜጎቹ ላይ የሽብር ተግባር መፈፀሙን አጣርቼ አረጋገጥኩኝ የሚል ነው፡፡ ልብ በሉ እንግዲህ “ጠበቃ”
ተማም በፅሁፉ እንደገለፀው እራሱ መረጃ ሰብስቦ፣ መርምሮና ደምድሞ ብይን ሰጠሁ ነው የሚለን፡፡
መች ይሄ ብቻ ፀጥታ አስከባሪውን ፖሊስ ዱርዬ፣ በጨዋ ደንብ ሐይማኖታዊ
ስርዓቱን አክብሮ በሰላም የሚሄደውን ህዝበ ሙስሊም ደግሞ እስልምና ውስጥ የተሰገሰገ ቦዘኔ ብሎ በመፈረጅ ፍርደ ገምድልነቱን ወይም
በተማም አጠራር የሕግ ባለሙያነቱ ገሃድ ወጥቷል፡፡ ጥብቅና ለቆመላቸውና ንፁህ ናቸው እያለ ለሚከራከርላቸው በሽብር ወንጀል ተጠርጥረው
በሕግ ቁጥጥር ስር ለሚገኙት ደንበኞቹ አጋዥ ይሆነኛል በሚል ሒሳብ ይመስላል እንዲሁ የፈጠራ ወሬውን መረጃ ሳይታክት በማሰራጨት
ላይ ተጠምዷል። እውነት እና ፈጠራ በሕግ ዓይን ምን ያህል የማይታረቁ አራምባና ቆቦ ቢሆኑም ለ”ጠበቃው” ተማም ግን ሁሉም ያው
ስለሆኑ ልፋት ወደማይጠይቀው አሉቧልታ በማዳላት አሉቧልታውን እፋፍሞታል። የተማም አባቡልጉ ጥብቅና እንግዲህ እንዲህ መሆኑን ነው
አይደል!
ፕሬሱ በልማትና ዕድገት ወሬዎች ላይ ሲጠመድ ሆድ የሚብሰው ተማም ከዚህም ከዚያም ጋር በሚያላትማቸው አጀንዳዎች የፀረ ሽብርተኝነት አዋጁን
ለንግግሩ ማሟሻነት በመጠቀም ቲፎዞ ለማሰባሰብ ስለ ጽሁፉ ይዘትና ብስለት እንኳ ከቁብ ሳይቆጥር እንዲሁ ይባዝናል፡፡ የተማም ጥብቅና
አልፋና ኦሜጋም በገዛ የራሱ ፅሑፍ እንዲሁ በተውረገረጉ አስተያየቶች እንካችሁ ትዕዝብት ይለናል።
አቶ ተማም የተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች መድርክ ላይ መንግስትን የሚተቹ
ፅሁፎችን በማቅረብም እናውቀዋለን። ያልተጨበጠ ወሬ አንጠልጥለው በመሮጥ ከሚታወቁት ልክ እንድሰማያዊ ፓርቲው ኢንጂነር ይልቃል የመሳሰሉ
ጥቂት መርህ የለሽ ግለሰቦች “ጠበቃ” ተማምም ነገር አንጠልጥሎ ወደ የግል የሕትመት ውጤቶች የመሮጥ አባዜ ከተጠናወተው ሰንበትበት
ብሏል። የተማም ጉድ ማለቂያ የለውምና ገና በክስ ሂደት ላይ ያለውን የፕሬሶችን ጉዳይ ፊቱን ወደ ቅጥፈት ጀርባውን ደግሞ ወደ እውነት
በማዞረ ሽንጡን ገትሮ በመከራከር የተከሰሱበትን ጭብጥ ለማድበስበስ ስለንፅህናቸው በማውራት በተለመደ የማጣመም እና የማውገርገር
አካሄዱን አሁንም ቀጥሎበታል። ለነገሩ እውነትና ተማም ሆድና ጀርባ ሆነው ከተለያዩ እንዲያውም ሰላምታ እንኳን ከተዘጋጉ ቆይተዋል።
እንዲያውም ተማም እውነት ወዳለችበት ስፍራ ዞር እንደማይል ያው በየጊዜው ለንባብ ከሚያበቃቸው ትንታኔ መሳይ ፅሑፎች እኛም ገብቶናል።
ተማም አባቡልጉ ጥብቅና የቆመላቸውና የፀረ ሽብርተኝነት ህጉን በመተላለፍ
የተከሰሱት “ደንበኞቹ” የፍርድ ሂደቱ በጋዜጣና በመፅሔት ላይ የሚካሔድ ይመስል ባልተገራ ብዕሩ የፀረ ሽብርተኝነት ህጉ እንዲሰረዝ
በየጋዜጣውና በየመፅሔቱ ደፋ ቀና ይላል፡፡ ይህን መልዕክቱን የሚያስተላልፍባቸው ሚዲያዎች ስለፈፀሙት እኩይ ተግባር ሆን ብሎ በመካድና
እውነቱን በማጣመም ያለሀፍረት ንፅህናቸውን ሊነግረን ይከጅለዋል። ከሎሚ መፅሔት ጋር ነሐሴ 10/16 ባደረገው ቃለ ምልልስ ህገ
መንግስታዊውን ስርዓት የናደው የኢትዮጵያ መንግስት ነው ብሎ ገና በፍርድ ሂደት እየታዩ ያሉትን ፕሬሶች ነፃ ናቸው ብሎ የሙያ ብቃቱን
አሳይቶናል። የኢትዮጵያን ህገ መንግስታዊ ስርዓት የናዱት የኢትዮጵያ ፕሬሶች ሳይሆኑ የኢትዮጵያ መንግስት ነው የሚል ድምዳሜውንም
ነግሮናል። በፍርድ ሂደት ውስጥ ያለን ነገር አስቀድሞ ወንጀለኛም ቢሆን ንፁህ ማለት ስለማይቻል በሕግ አገላለፅ ተጠርጣሪ የሚባል
ስም እንደሚሰጠውና ነፃ ወይም ወንጀለኛ የሚባል ስያሜ የሚሰጠው ደግሞ በፍርድ ሂደቱ የጥፋተኝነት ብይን ከተሰጠ በኋላ ፍርድ ቤቶች
በሚሰጠት ውሳኔ ሆኖ ሳለ የ”ሕግ ባለ ሙያ”ው ተማም ግን በተቃራኒው ከፍርድ ሂደቱ ቀድሞ ውሳኔውን ለማደናቀፍ በሚያስችለው መልኩ
ስለንፅህናቸው ይነግረናል። ይሄ ነው እንግዲህ “ጠበቃው” ጎበዝ!
የተማም ጥየቄ የፀረ ሽብርተኝነት አዋጁ ላይ ያነጣጠረ ለመሆኑ ከየአጀንዳው
ጋር እየለጠፈ በሚያስተላልፋቸው መልዕክቶች መረዳት ይቻላል፡፡ ምን ይሄ ብቻ ተማም የፀረ ሽብርተኝነት ህጉን ተላልፎ የተገኘን ሁሉ
መልአክ አድርጎ በመሳል አሊያም በጀግንነት በመፈረጅ ሽብርን በግላጭ ያበረታታል። ለማንኛውም ፀረ ሽብርተኝነት ህጉ ሽብርንና ሽብርተኞችን
የሚያሳድድና ንፁሃን ዜጎች ደግሞ በሰላም ወጥተው በሰላም እንዲገቡ ዋስትና የሚሰጥ እንደሆነ ሁላችን በአግባቡ እንገነዘባለን። ተማም
ታዲያ ለምን ይደነብራል የሚል ጥያቄ ማንሳትም ተገቢ ይመስለኛል። ነው ወይስ------? ልለፈው መሰለኝ።
“ጠበቃ” ተማም የሕግ ባለሙያ ሆኖ ከሕግ ጋር የመጣረስና ከእውነት ጋር
የመፋታት ምስጢሩ ያለህ የተዛነፈ ፖለቲካዊ እይታ እንጂ ሌላ ነገር እንዳልሆነ በየጊዜው ለንባብ ከምታበቃቸው ፅሑፎች መረዳት ችያለሁ።
ሌላውን አካል ፅንፈኛ ብለህ ከመፈረጅህ በፊት ደግሞ አንተ የያዝከውን ጭፍን ፅንፍ ጠንቅቀህ ብትረዳው መልካም ነው፡፡ ለነገሩ ያን
ያህል ለመረዳት ዝግጁ መሆን በራሱ ከእውነት ጋር መታረቅን ስለሚያስከትል እንደማይመለከትህ ቢገባኝም እንደው ብትባንን ለማለት ነው!
በየጊዜው ባልተገራ ብዕርህ የሚታብጠለጥለው መንግስትና ህገመንግስት ነው እንግዲህ እንደልብ ለመፈንጨት ጭምር መብትና ነፃነትም ያጎናፀፈህ።
አጠቃላይ የ”ጠበቃ” ተማም ጥብቅና ለሕግና ለስርዓት ሳይሆን ሕግና ስርዓት ለማፍረስ ለተሰለፉ አፍራሽ ኃይሎች ስለመሆኑ ከራሱ ከተማም
ፅሑፎች በመነሳት መደምደም ይቻላል። ይህም ጥብቅና መሆኑን ግን እያወቅን ነው!
No comments:
Post a Comment