Tuesday, August 19, 2014

የኢትዮጵያ ልዑካን ቡድን በአሜሪካ የነበረው ቆይታ የተሳካ እንደነበረ ተገለፀ

አሁን ባለን የአፈፃፀም ደረጃ የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅዳችንን ለማሳካት በሚቻልበት መንገድ ላይ ሲንሆን የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በአሜሪካ በሚኖሩ ኢትዮጵያውያን፣ ትውልደ ኢትዮጵያውያንና በአሜሪካ ኩባንያዎች ዘንድ የኢንቨስትመንት ፍላጎት ማሳደር መቻሉም ተጠቅሷል።

በኢትዮ-አሜሪካ የኢንቨስትመንት ፎረመና በአፍሪካ-አሜሪካ ኢኮኖሚ ትብብር መድረክ ላይ ለመሳተፍ ወደ አሜሪካ ያቀናው በኢፌደሪ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ሙላቱ ተሾመና በኢፌደሪ ጠቅላይ ሚንስትር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ የተመራው የኢትዮጵያ ልዑካን ቡድን በአሜሪካ በነበረው ቆይታ ኢትዮጵያ እያከናወነች ያለውን ውጤታማ ተግባር ያስተዋወቀችበትና ለአፍሪካውያን አጋሮቿም ተሞክሮ ያስተላለፈችበት እንደነበረ የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት አስታወቀ፡፡
የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ኃላፊ ሚኒስትር አቶ ሬድዋን ሁሴን እንዳብራሩት በአሜሪካ የሚገኙ ትላልቅ ኩባንያዎች  ወደ ሃገራችን ባለሙያ በመላክ ጭምር በኢንቨስትመንት መስክ ለመሰማራት የሚያስችላቸውን ጥናት እያደረጉ መሆኑን የገለፁ ሲሆን ይህ የሃገራችን ኢኮኖሚ የፈጠረው ፍላጎት ነው ብለዋል፡፡  ሚኒስትሩ አያይዘው ይህ ፍላጎት የሀገር በቀል ኩባንያዎች ምርታቸውን የሚቀበል ገበያ እንዲያገኙ እድል ከመክፈቱ ባሻገር በሽርክና ለመስራትም የሚያስችል መልካም እድል ነው ብለውታል፡፡
በአሜሪካ የሚኖሩና ግዙፍ ኩባንያዎች ውስጥ ተቀጥረው በመስራት አንቱ የተባሉ ዜጎቻችን ሃብት በመቋጠር ለኢትዮጵያ ጠቃሚ ነገር ለመስራት ማሰብ የጀመሩበትና እውነተኛ ፍላጎት ያሳዩበት ሁኔታ እንዳለና በሀገራችን እየተመዘገበ ያለው ለውጥም ለዲያስፖራው መነሳሳት የፈጠረ እንደሆነ ልዑኩ በነበረው ቆይታ ማረጋገጡን አቶ ሬድዋን አስረድተዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም በተገኙበት መድረክም ኢትዮጵያ ከአሜሪካ ጋር በጋራ መድረኩን የመምራት እድል የተሰጣት ሲሆን በተጨማሪም በጤና፣ በተፋሰስ ልማት ስራ፣ የግብርና ምርትና ምርታማነትን በመጨመር፣ በሴፍትኔት ፕሮግራም ትግበራ ያስመዘገበቻቸውን ስኬታማ ተግባራት እንድታቀርብ መደረጉን አቶ ሬድዋን በመግለጫቸው ጠቁመዋል፡፡ መድረኩ ኢትዮጵያ ልምዷን ያካፈለችበት ከሌሎች ሃገራት ልምድ የወሰደችበት በመሆኑ የተሳካ ነበር ብለዋል ሚኒስትሩ፡፡
አቶ ሬድዋን የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ የመጨረሻ ዓመት ላይ በመሆናችን ባለፉት ዓመታት በርካታ ግዙፍ ተግባራትን ያከናወንን ቢሆንም የተንጠባጠቡና ተረባርበን የምናሳካቸው ተግባራት እንዳሉ ሆነው አሁን ባለን የአፈፃፀም ደረጃ እቅዱን ለማሳካት በሚቻልበት መንገድ ላይ ነን ብለዋል፡፡ እቅዱ ተለጥጦ የታቀደና የተለጠጡ ግቦች ያሉት እንደሆነ መዘነጋት እንደሌለበትም አስታውሰዋል፡፡
በህግ የተጠየቁ የግል ፕሬሶች ከምርጫ ጋር በተያያዘ ነው በሚል ከጋዜጠኞች ጥያቄ የቀረበላቸው ሲሆን አቶ ሬድዋን እነሱን ለመክሰስ በቂ ምክንያት እንዳለ በመጠቆም ማንም ይሁን ማንም ሃገር የሚያተራምስ ከሆነ ምርጫ ቢኖርም ባይኖረም የህግ የበላይነትን ማረጋገጥ የማይቀር የመንግስት ተግባር መሆኑን አስረድተዋል፡፡     
መንግስት ይህን እርምጃ የወሰደው ነገሩን በሆደ ሰፊነት በመመልከት የተለያዩ ማስተካከያዎችን አስቀድሞ ለመውሰድ ከጣረ በኋላ መሆኑን የተናገሩት አቶ ሬድዋን ይህ የመንግስት ሆደ ሰፊነት ገደቡን ሲያልፍ ኃላፊነትን ያለመወጣት ስለሚሆን አጀንዳቸው፣ የጥፋታቸው ዓይነትና ብዛትን ሚዛን በማስገባት የተወሰደ ሕጋዊ እርምጃ መሆኑን አብራርተዋል፡፡             
የኢትዮጵያና የግብፅ ድርድርን በተመለከተ አቶ ሬድዋን ከጋዜጠኞች ጥያቄ የቀረበላቸው ሲሆን ድርድሩ የሚቀጥል መሆኑን በመግለፅ የእኛ ራዕይና አቋም ግልፅ ነው ብለዋል፡፡ ኢትዮጵያ መቼም ቢሆን የግብፅ ህዝብ ጥቅም ለመጉዳት ሰርታ አታውቅም ያሉት ሚኒስትሩ ወደ ግብፅ የሚፈሰው ውሃ አሁንም ፍሰቱን ጠብቆ ይቀጥላል ነው ያሉት አቶ ሬድዋን፡፡ ከአቋማችን ጋር የሚጋጭ ነገር ቢመጣ አንደራደርም በማለትም የመንግስትን አቋም አስገንዝበዋል፡፡

በተቃዋሚዎች በኩል አባሎቻችን እየተሳሩብን ነው በማለት የሚቀርበውን ክስ አስመልክቶም አቶ ሬድዋን ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ የሰጡ ሲሆን ጉዳዩ በግል የሚፈፀሙ ህግን የጣሱ ተግባራት በመሆናቸው በግሉ ህግ የሚጥስ ካለ መጠየቁ የማይቀርና የህግ የበላይነትን የማረጋገጥ ጉዳይም የገዥው ፓርቲ ብቻ መሆን እንደሌለበት አስረድተዋል፡፡

No comments:

Post a Comment