Sunday, August 9, 2015

የኢህአዴግ ምክር ቤት የ10ኛው ድርጅታዊ ጉባኤ ረቂቅ ሪፖርትን ገምግሞ ለጉባኤው እንዲቀርብ በመወሰን መደበኛ ስብሰባውን አጠናቀቀ

የኢህአዴግ ምክር ቤት ከነሃሴ 1-2 ቀን 2007 ዓ.ም ባካሄደው መደበኛ ስብሰባው  የመጀመሪያውን የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ አፈጻጸምና የ9ኛው የኢህአዴግ ጉባኤ ውሳኔዎች መሰረት በማድረግ የተዘጋጀውን ረቂቅ ሪፖርት በዝርዝር በመገምገም ለ10ኛው የድርጅቱ ጉባኤ እንዲቀርብ መወሰኑን የኢህአዴግ ምክር ቤት ጽሕፈት ቤት አስታወቀ፡፡
የመጀመሪያው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ለሁለተኛው የእቅድ ዘመን መነሻ የሚሆኑ ልምዶችና ትምህርት የተገኘበት መሆኑን የገመገመ ሲሆን በእቅድ አፈጻጸሙ የነበሩ ስኬቶችን ለማስፋት እንዲሁም የነበሩ ችግሮችንና ተግዳሮቶችን ትኩረት ሰጥቶ ለመፍታት የተደረገውን ርብርብ ተኩረተ ሰጥቶ ተወያይቷል። የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ አፈፃፀሞችን በዝርዝር የገመገመው ምክር ቤቱ በመጀመርያዎቹ አራት አመታት የ10 ነጥብ 1 በመቶ የተመዘገበ  መሆኑን የገመገመው ምክር ቤቱ  እድገቱ ሀገራችን በአለም አቀፍ ደረጃ  እጅግ ፈጣን ዕድገት እያስመዘገቡ ካሉ ጥቂት ሀገራት አንዷ እንድትሆን ያስቻለ ስኬት መሆኑን አረጋግጧል።
የእድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅዱን የልማት ሃይሎችን በተቀናጀና በተደራጀ መልኩ በማንቀሳቀስ በልማት ሰራዊት ግንባታ አቅጣጫ መፈጸሙ ስኬታማ አፈጻጸምና እንዲኖርና የልማት ሃይሎች ዓቅም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጎለበተ እንዲመጣ ያደረገ በመሆኑ ተጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባው ምክር ቤቱ አስምሮበታል።
በገጠር የልማት ሰራዊት ግንባታው  በተለይም በተፈጥሮ ሃብት ልማት በየዓመቱ በሚልዮኖች የሚቆጠር ህዝብ አካባቢውን ለማልማት ያደረገው ርብርብ ውጤታማና ለቀጣይ ስራም የተሻለ ልምድ የተገኘበት መሆኑን የተመለከተው ምክር ቤቱ በመስኖ ልማትም እያንዳንዱ አርሶ አደር አማራጭ የውሃ ዕቀባ ዘዴ እንዲኖረው ለማድረግ የታየዘው ዕቅድ አፈፃፀም በሚፈለገው ደረጃ ባይሆንም በአጠቃላይ የመስኖ ስራው ግን ለቀጣይ ስራ ትምህርት የተገኘበት እንደሆነ ምክር ቤቱ አይቷል። በገጠር በሌሎች የትምህርትና የጤና ልማት መስኮችም የሰራዊት ግንባታውን አጠናክሮ ለማስቀጠል የሚያስችል ሰፊ ልምድ የተገኘበት በመሆኑ ለቀጣይ የዕቅድ ዘመን አመቺ ሁኔታዎች መፈጠራቸውን ገምግሟል። በከተማ የልማት ሰራዊት ግንባታ ረገድም በትምህርትና በአነስተኛና ጥቃቅን ተቋማት መስኮች በመልካም ተሞክሮነት የሚወሰድ ሆኖ የህዝቡን ተሳትፎና ተጠቃሚነት መሰረት ያደረገና በቀጣየ ተጠናክሮ መቀጠል ያለበት አፈፃፀም መመዝገቡን በዝርዝር የፈተሸው ምክር ቤቱ በመልካም አስተዳደር ረገድ በተለይም በሲቪል ሰርቪስና በፍትሕ መስክ ግን የተመዘገበው መሻሻል እንደተጠበቀ ሆኖ የህዝቡን እርካታ ያላረጋገጠ በመሆኑ የታዩ ጉድለቶች በቀጣይ ትኩረት የሚሻ እንደሆነ ምክር ቤቱ አፅንኦት ሰጥቶ ተወያይቶበታል።
ባለፉት 12 ዓመታት የተመዘገበውን ፈጣን፣ ተከታታይና በየደረጃው የህዝቡን ተጠቃሚነት እያረጋገጠ የሚገኘውን እድገት ለማስቀጠል የኢኮኖሚው መዋቅራዊ ለውጥና ትራንስፎርሜሽን የቀጣይ ትኩረት እንደሚሆንና በማኑፋክቸሪንግና በኤክስፖርት ንግድ የነበረው ዝቅተኛ አፈፃፀም ትኩረት ሰጥቶ ሊፈታ እንደሚገባ ምክር ቤቱ አፅንኦት ስጥቶበታል።
የዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ አፈፃፀምን በዝርዝር የገመገመው ምክር ቤቱ የዴሞክራሲ ስርዓታችን ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጎለበተ መጥቷል ብሏል። በዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ስራው ምሶሶ የሆኑት የህዝብ ምክር ቤቶች ሕግ የማውጣትና አስፈፃሚውን አካል የመቆጣጠር ዓቅም በቀጣይነት እየተሻሻለ የመጣ ቢሆንም በቀጣይ ህዝቡን ይበልጥ እያሳተፉ ለመሄድ ርብርብ እንዲያደርግና ለምክር ቤቶች ተጠሪ የሆኑ ዴሞክራሲያዊ ተቋማት፣ ህዝባዊ ማሕበራት፣ ሚዲያና የመሳሰሉ ተቋማት ለዴሞክራሲያዊ ስርአት ግንባታ ሚናቸው ይበልጥ ሊጠናከር እንደሚገባ ተመልክቷል።
አምስተኛው ጠቅላላ ምርጫ ከፍተኛ የህዝብ ተሳትፎ በተረጋገጠበት ነፃ፣ ፍትሃዊ፣ ዴሞክራሲያዊና ሰላማዊ ሆኖ መጠቃለሉን የተመለከተው ምክር ቤቱ ህዝቡ ለኢህአዴግ የሰጠውን ከፍተኛ ኃላፊነት በብቃት ለመወጣት መላ የድርጅቱ አመራርና አባላት በቁርጠኝነት ሊንቀሳቀሱ እንደሚገባ አስምሮበታል፡፡ የመድብለ ፓርቲ ዴሞክራሲያዊ ስርዓቱን ይበልጥ አሳታፊ በማድረግ አጠናክሮ ለማስቀጠል የምክር ቤቶችና የዴሞክራሲ ተቋማትን አቅም የማጎልበትና የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤትን በማጠናከር የፓርቲዎቹን ተሳትፎ ማረጋገጥ በቀጣይ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ ገምግሟል።

በመጨረሻም ምክር ቤቱ በያዝነው ወር የሚካሄደው የኢህአዴግ 10 ድርጅታዊ ጉባኤ የሚቀርበውን ሪፖርት በመጀመርያው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ አፈጻጸም የተገኙ ልምዶችን መነሻ በማድረግና ህዝቡ በ5ኛው ጠቅላላ ምርጫ ለኢህአዴግ የሰጠውን ከፍተኛ ኃላፊነት መሰረት በማድረግ በቀጣይ አመታት የላቀ እድገትና ትራንስፎርሜሽን ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ዋናዋና አቅጣጫዎችን አካቶ የተዘጋጀ መሆኑን በማረጋገጥ በምክር ቤቱ ውይይት ወቅት የተነሱ ሃሳቦችን አካቶ ለጉባኤው እንዲቀርብ በመወሰን ስብሰባውን ማጠናቀቁን የኢህአዴግ ምክር ቤት ጽሕፈት ቤት በላከው መግለጫ አስታውቋል።

No comments:

Post a Comment