Tuesday, August 4, 2015

የቤት ስራችንን በመስራታችን የተሰጠን እውቅና


ከአሜሳይ ከነዓን
የጥንታዊ ስልጣኔ ባለቤት የሆነችው ኢትዮጵያ  በማናቸውም ጊዝያቶች በውጭ ወራሪ ሃይላት ያልተንበከከችና ለዘመናት ሉአላዊነቷን ጠብቃ የቆየች ሀገር ናት። ሁሉም የአፍሪካ ሀገራት በቅኝ ግዛት ስር በወደቁበት ጊዜም ከየአቅጣጫው የተደቀኑባትን ወረራዎች በብቃት በመመከት የራሷን ሉአላዊነት ከመጠበቅ ባሸገር ለሌሎች የነፃነት ታጋዮችም የአይበገሬነት ተምሳሌት በመሆን ታግሎ ማሸነፍ እንደሚቻል በተግባር ያስተማረች ነች ሀገራችን።

የኢትዮጵያና የአሜሪካ ሁለትዮሽ ግንኙነትም የተጀመረው አብዛኞቹ የአፍሪካ ሀገራት በቅሽ ግዛት ስር በነበሩበት ዘመን ነበር፡፡ እናም ግንኙነቱ እ.አ.አ ከ1903ዓ.ም ጀምሮ አንዴ ዝቅ ሌላ ጊዜ ደግሞ ሞቅ እያለ መጥቶ በአምባገነኑ የደርግ ስርዓት በጎሪጥ እስከመተያየት ደርሶ ነበር። ለዚህ ግንኙነት መቋረጥ ደግሞ ደርግ የተከተለው የተሳሳተ የውጭ ግንኙነት አቅጣጫ ሲሆን ይህም ስርዓቱ የሶሻልዝም ርእዮተዓለም እከተላለሁ በማለት የጀመረው ፀረ-አሜሪካ ፕሮፓጋንዳ ነበር።
ከደርግ ወድቀት ማግስት በዴሞክራሲያዊ ሁኔታ ህዝባዊ  ስልጣን የተረከበው ኢህአዴግ በጋራ ጥቀም ላይ የተመሰረተና ማንንም በወዳጅነት ማንንም በጠላትነት የማይፈርጅ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ በመቅረፅ ኢትዮጵያ ከአለም ሀገራት ጋር ያላት ግንኙነት በእኩልነትና በመከባበር ላይ እንዲመሰረት እልህ አስጨራሽ ትግል አድርጓል።ከአሜሪካ ጋር ለ17 ዓመታት ያክል ተቋርጦ የነበረውንም ግንኙነት በተሻለ ሁኔታ በማስቀጠል እንዲጠናከር አድርጓል፡፡

ሀገራችን ራሷን በምስራቅ አፍሪካም ይሁን በመላው አለም ለቱሪዝምና ለኢንቨስትመንት የተመቸች፣ በተለያዩ የዓለማችን አካባቢዎች የሚገኙ ባለሃብቶች መዋእለንዋያቸውን  ኢንቨስት ለማድረግ የሚመርጧትና በተለይ ወትሮ ትታወቀበት ከነበረውና ሁሉንም ኢትዮጵያዊ አንገት ከሚያስደፈው የረሃብ፣የኋላቀርነትና የጦርነት ታሪኳ ተላቃ በራሷ ዓቅም መቆም የምትችል ዴሞክራሲያዊት ሀገር ለመገንባት ባለፉት ሁለት አስርት አመታት ያለመታከት ተሰርቷል፡፡

ኢህአዴግ በቀየሳቸው ትክክለኛ ተኮር ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች ከራሳችን አልፈን አለም በእኛ ለውጥ እንዲያምን ያስገደደ ፈጣንና ተከታታይነት ያለው ፍትሐዊ እድገት ተመዝግቧል፡፡ አገራችን ከፈጣን እድገቷ ባሻገር የተረጋጋና ዘላቂ ሰላም ያለባትም አገር ለመሆን በቅታለች፡፡ ከውስጣችን አልፈን የፍሪካውያን ወንድሞቻችንን ሰላም ለመጠበቅም ከፍተኛ መስዋእትነት እየከፈልን ያልተቆጠበ ጥረት በማድረግ ላይ እንገኛለን፡፡

ይህ ሁለንተናዊ ለውጣችን ታዲያ ሀገራችን ስሟ በዓለም አቀፍ መድረኮች የሚጠራው በተመፅዋችነቷን ሳይሆን በልማት አጋርነቷንና በኢንቨስትመንት መዳረሻነቷን እንዲሆን አስችሏል። የወጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት በመሳብ ረገድም አሁንም ብዙ መስራት የሚጠበቅብንና ከዘርፉ የተሻለ ጥቅም ለማግኘት የሚያስችለን ምቹ ሁኔታ መፍጠር ያለብን ቢሆንም እስካሁን የተገኙ ልምዶችን ግን ሀገራችን የሚያበረታታ ውጤት በማስመዝገብ ላየ ትገኛለች።  ዛሬ የቱርክ፣ ህንደና ቻይና ግዙፍ ኩባንያዎች ባሻገር የአውሮፓውያንና የአሜሪካዊያን ባለሃብቶችንም በአገራችን መዋለ ነዋያቸውን በማፍሰስ ላይ ይገኛሉ፡፡ ይህ ሁሉ ደግሞ በተከተልነው ትክለኛ የዕድገት አቅጣጫ የተገኘ ስኬት ነው።

አገራችን ኢትዮጵያ የተለጠጠና ወደተሻለ የእድገት ምዕራፍ ሊያሸጋግረን የሚችል የአምስት ዓመት የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ በማውጣት የምእተ ዓመቱን  የእድገት ግቦች እንዲሳኩ ከማንም በላይ በቁርጠኝት በመትጋት ላይ ያለች ሀገር ናት፡፡ በዚህም በምእተ ዓመቱ  የእድገት ግብ የተቀመጡ ተግባራትን  በማሳካት ዓለም በአንድ ድምፁ ቁርጠኝነቷን እንዲመሰክርላት ሆኗል፡፡ የህፃናት ሞትን ለመቀነስ የተያዘውን እቅድ ቀድማ አሳክታለች፡፡ የእድገት ግቡ መጀመሪያ ላይ የነበረውን የ46 በመቶ የድህነት መጠን ወደ 22 በመቶ በማወረድ በርካታ ሚሊዮን ዜጎቻችን ከድህነት አረንቋ እንዲወጡ በማስቻል አንፀባራቂ ድል ተመዝግቧል፤ አሁንም የእነዚህ በድህነት ውስጥ የሚኖሩ ዜጎቻችን ህይወት ለመለወጥ ቀጣይ ርብርብ ማድረግ ያለብን ቢሆንም፡፡

ይህ ሁሉ የሚያሳየው አገራችን ከድህነት ለመላቀቅ ያላትን ቁርጠኝነት ነው፡፡ ለዚህም ነው በዓለም አቀፍ ደረጃ ከኢትዮጵያ ጋር በአጋርነት መስራት እንደ ጥሩ አጋጣሚ እየተወሰደ ያለው። የተለያዩ አለምአቀፍ መድረኮችን በማዘጋጀት እውቅናን ያተረፈችው አገራችን በያዝነው በ2007 ዓ.ም  ሶስተኛውን አለምአቀፍ የፋይናንስ ለልማት ጉባኤ በማዘጋጀትም አቅሟንና የልማት አጋርነቷን በተግባር አረጋግጣለች፡፡ የተመድ ኢኮኖሚና ማህበራዊ ጉዳዮች ጀነራልና የሶስተኛው አለምአቀፍ የፋይናንስ ለልማት ጉባኤ ሴክሬታሪ ጀነራል ዉ ሆንግቦ ጉባኤው ከመካሄዱ በፊት በኢትየጵያ የሚካሄደው ጉባኤ ተገቢነቱን በማመላከት በአገሪቱ እየተመዘገበ ያለው ፈጣንና ተከታታይነት ያለው ፍትሐዊ እድገት ጉባኤን በስኬታማነት እንድታዘጋጅ ያግዛታል ሲሉ ተደምጠዋል፡፡

በእርግጥም ከኳታርና ከሜክሲኮ በኋላ በሶስተኛናት አገራችን የአለም አበዳሪ ተቋማትና መሪዎች የተገኙበትን ጉባኤ በስኬታማነት በማጠናቀቅ ያለችበትን ሁለንተናዊ የለወጥ ቁመና በተጨባጭ ማሳየት ችላለች፡፡ የሐምሌ ወር የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ባራክ ሁሴን ኦባማ ጉብኝትም ይህችን አለም ለውጧን እየመሰከረላት ያለችውን ብሩህ ተስፋዋን ፍንትው ብሎ የሚታየው አገር እውቅና መስጠት ተገቢና ወቅታዊ ነው የሚል እምነት አለኝ፡፡ የፕሬዝዳንቱም ይፋዊ ጉብኝት የኢትዮጵያና የአሜሪካ ስትራቴጂክ ግንኙነት ሁለቱንም አገራት የሚጠቅምና በመተማመንና መደጋገፍ ላይ የተመሰረት እንዲሆን የሚያግዝ ነው፡፡


አሜሪካ በሀገራችን እየተመዘገበ ያለው ሁለንተናዊ እድገት አስተማማኝና ቀጣይነቱም የማያጠራጥር እንደሆነ በማመኗ ግንኙነቷን ማጠናከሯና ለሀገራችን ለውጥም እውቅና መስጠት ተገቢ ነው፡፡ በአገራችን ባለፉት ዓመታት የተዘመገቡት የሰላም የልማትና የዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ እመርታዎች አሜሪካን ጨምሮ በርካታ ሀገሮች ሀገራችንን ተመራጭ እንዲትሆን አስችሏል፡፡ ይህ ማለት ግን ሁሉ ነገር አበቃለት ማለትም አይደለም፡፡ በጀመርነው ፍጥነት በመቀጠል ሀገራችን ከድህንት ተላቃ መካከለኛ ገቢ ካላቸው ሀገራት ተርታ ማሰለፉ በከፍተኛ ቁርጠኝነት መስራታችን አጠናክረን መቀጠል ይኖርብናል። ኦባማ በጉብኝታቸው ወቅት እንደገለፁት 100 ፐርሰንት ትክክል የሚባል ዴሞክራሲ የትም የለም፤ በሀገረ አሜሪካም ቢሆን፡፡ ለውጡም እንዲሁ በአንድ ጀምበር ዳር ማድረስ አይቻልምና ሁሉም የራሱን ጊዜና ጉልበት ይፈልጋል፡፡ የሀገራችን አርሶና አርበቶ አደሮች፣ ኢንዱስትሪያሊስቶች፣ ባሃብቶች፣ ወጣቶችና ሴቶች ሁሉም በጋራ ሲተባበሩ ነገ ከበድ ያለውን የቤት ስራ ከመስራት የሚያግዳቸው አንዳች ሃይል እንደሌለ የእስካሁን ስኬታቸው ዓይነተኛ ማሳያ ተደርጎ የሚወሰድ ነው። ዛሬ ትናንት ያሰፈርነውን የቤት ስራችንን በአግባቡ በማጠናቀቃችን አለም ድጋፉን እድገታችንን እውቅና በመስጠት እያሳወቀን ነው፡፡ ነገ ደግሞ የተሻለችሀገር፣ የተሻልን ህዝቦች ሆነን በዓለም አደባባይ አንገታችን ይበልጥ ቀና ለማድረግ አሁንም እንደ ትናንቱ ልማት፣ ሰላምና ዴሞክራሲ የህልውናችን መሰረቶች ናቸው ብለን ከፍተኛ ርብርብ ማድረግ ይኖርብናል፡፡ ሰላም፡፡       

No comments:

Post a Comment