የተከበራችሁ የሀገራችን ህዝቦች!
ከሁሉም በማስቀደም አምባገነናዊ ስርዓት ለተወገደበት የትግላችሁ ውጤት ለሆነው የ23ኛው የግንቦት 20 ድል እንኳን አደረሳችሁ።
የግንቦት 20 ድል በሀገራችን ለዘመናት ተንሰራፍቶ የነበረውን የዓፈናና የጭቆና ስርዓት የተወገደበትና በምትኩ ልማታዊና
ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ለመገንባት የሚያስችል ፅኑ መሰረት የተጣለበት
በመሆኑ ልዩ ቦታና ክብር ይሰጠዋል። የሀገራችን ህዝቦች
ለዘመናት የተዋደቁለት የሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶችና ነፃነቶች በተለይ ደግሞ የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች እኩልነት የማረጋገጥ
ቁልፍ ጥያቄ ምላሽ ያገኘበት ታላቅ ድል ነው።
የግንቦት 20 ድል ሀገራችን በግልፅ ተደቅኖባት የነበረውን የመበታተን አደጋ በመታደግ የኋልዮሽ ጉዞዋን በአስተማማኝ
ሁኔታ በመቀልበስ ድሮ ወደነበረችው የስልጣኔ ማማዋ ለመመለስ የሚያስችል በህዝቦች ይሁንታና መከባበር ላይ የተመሰረተ የዴሞክራሲያዊ
ስርዓት መሰረት የተጣለበት የህዳሴአችን ጮራ የፈነጠቀበት ድላችን ነው።
የተከበራችሁ የሀራችን ህዝቦች!
23ኛው የግንቦት 20 የድል በዓል ስናከብር ያለፈው የትግል ታሪክና የከፈልነው መስዋእትነት ከማስታወስ
ባሻገር በትግላችን የተጎናፀፍናቸው መብቶችና ነፃነቶች ይበልጥ ለማጎልበትና ለማጠናከር እንዲሁም ሀገራችን በማስመዝገብ ላይ የሚትገኘውን
የኢኮኖሚ ዕድገት ወደ ከፍተኛ ደረጃ በማሸጋገር የሀገራችን ህዳሴ
ዳር ለማድረስ ቃላችን በማደስ መሆን ይገባዋል።
ባለፉት 23 ዓመታት ጉዞአችን የሀገራችን ህዳሴ ለማረጋገጥ ብሩህ ተስፋ ያመላከቱ የልማት፣ የሰላምና የዴሞክራሲ ስኬቶች
ማስመዝገብ ችለናል። ለሀገራችን ህዳሴ አስተማማኝ መሰረት ይሆናል ተብሎ የታመነበትን የአምስት ዓመቱ የዕድገትና ትርንስፎርሜሽን
ዕቅዳችን ከአንድ የስኬት ምዕራፍ ወደ ቀጣዩ ከፍተኛ የስኬት ምዕራፍ እያሸጋገረን ይገኛል። ሀገራችን እጅግ ፈጣን ዕድገት ከሚያስመዘግቡ
ጥቂት የዓለም ሀገሮች አንዷ መሆን ችላለች። ይህ ፈጣን ዕድገት ባለፉት 10 ዓመታት በተከታታይ በአማካይ ባለ ሁለት አሃዝ ዕድገት
ያዝመዘገበና የህዝቦችን ተጠቃሚነትም ያረጋገጠ ነው።
የግብርና መር የኢንዱስትሪ ልማት ስትራቴጂ ቀርፀን ባደረግነው ከፍተኛ ርብርብ የህዝባችን ተጠቃሚነት በማረጋገጥ ላይ
እንገኛለን። በንጉሱ ዘመን የመሬት ባለቤትነት መብቱ ተነፍጎ በደርግ ዘመንም
ምርቱን የሚያሳድግበት ምንም ድጋፍ ባለማግኘቱና ያመረተውን ምርትም በተለያዩ ስልቶች በስርአቱ እየተመዘበረ ሲማቅቅ የነበረው የሀገራችን
አርሶ አደር በግንቦት 20 በተጎናጸፈው ድል አማካኝነት ምርትና ምርታማነቱን በከፍተኛ ደረጃ እያሳደገ ለኢኮኖሚ ዕድገታችን ከፍተኛ
አስተዋፅኦ እያደረገ ይገኛል፡፡
በከተማ ልማት በተለይ ደግሞ በአነስተኛና ጥቃቅን ተቋማት ልማት ዘርፍ እየተመዘገቡ ያሉ ስኬቶች የበርካታ ዜጎች ተጠቃሚነት
እያረጋገጡ ይገኛሉ። በተለይ ስራ ፈላጊ ወጣቶችና ሴቶች በማደራጀት በእነዚህ ተቋማት በማሳተፍ ከስራ አጥነት ወደ ስራ ፈጣሪነትና
የስራ ባለቤትነት ከማሸጋገሩ በተጨማሪ ፍትሐዊ የሃብት ክፍፍል በማረጋገጥ፣የዕውቀትና ክህሎት ዓቅማቸው በቀጣይነት በመገንባት የሀገራችን
የኢንዱስትሪ ሽግግር በማቀላጠፍ ረገድም ውጤቶች በማስመዝገብ ላይ ይገኛሉ።
በማሕበራዊ ልማት ዘርፍም እንደዚሁ ከፍተኛ ስኬቶች እየተመዘገቡ ይገኛሉ። የትምህርትና የጤና አቅርቦትና ተደራሽነት በማረጋገጥ
በኩል ረዥም ርቀት ተጉዘናል። በመሆኑም ዕድሜአቸው ለትምህርት የደረሱ የሀገራችን ዜጎች በቅርብ ርቀት የትምህርት አገልግሎት እንዲያገኙ በማድረግ በዕውቀትና በዘመናዊ አስተሳሰብ የዳበረ ትውልድ የመገንባት ዕቅዳችን
በስኬቶች እየታጀበ ነው። የትምህርት ጥራት በማረጋገጥም ፓኬጀፖች ቀርፀን በመረባረባችን ስኬቶች እየተመዘገቡ ይገኛሉ።መከላከልን
ማዕከል ባደረገው የጤና ፖሊሲያችንም እንዲሁ አመርቂ ውጤቶች በማስመዝገብ ላይ ይገኛል።
ባለፉት 23 ዓመታት ለኢኮኖሚ
ልማታችን ወሳኝ በሆነው የመሰረተ ልማት ዘርፍ ትኩረት ሰጥተን ተንቀሳቅሰናል። በመንገድ፣ በኤሌክትሪክ ኃይል፣ በቴሌኮሙዩኒኬሽ እና በመሳሰሉት ስኬቶች ተመዝግበዋል።
በመሰረተ ልማትም ሆነ በሌሎች ዘርፎች የነገይቱ ኢትዮጵያ የዕድገት አቅጠጣጫ በአግባቡ ያገናዘቡ
ሜጋ ፕሮጀክቶቻችን በተቀመጠላቸው አቅጣጫ መሰረት እየተከናወኑ ይገኛሉ።
ከእነዚሁ አንዱ የሆነው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ግድብ በከፍተኛ ህዝባዊ መነሳሳትና ተሳትፎ
ግንባታው እየተፋጠነ ሲሆን ለዘመናት ስር ሰዶ የቆየውን የአይቻልምና የበታችነት መንፍስ በመሰረቱ በመቀየር በህዝባችን ውስጥ አዲስ
የይቻላል እና የአሸናፊነት መንፈስ በመገንባት ሁሉም የሀገሪቱ ህዝቦች በአንድነት ማስተሳሰር ያስቻለን ፕሮጀክት ሆኗል። በቀጣይም
ኢህአዴግ እና ሁሉም የሀገሪቱ ህዝቦች እጅ ለእጅ ተያይዘው ታላቁ የህዳሴው ግድብና ሌሎች የልማት ዕቅዶቻችን በአግባቡ በማሳካት
ህዳሴአችን እውን ማድረግ እንደምንችል ኢህአዴግ በፅኑ ያምናል።
የተከበራችሁ የሀገራችን ህዝቦች!
ሀገራችን ባለፉት 23 ዓመታት በሁሉም የልማት ዘርፎች በርካታ ስኬቶች በማስመዝገብ ወደ ፊት እየገሰገሰች ብትሆንም ለዘመናት
ስር ሰዶ ከነበረው አስከፊ ድህነት፣ ኋላቀርነትና የዴሞክራሲ እጦት አንፃር አሁንም ድህነትን ሙሉ በሙሉ ስላላሰሸነፍነው የጀመርነውን
ልማትና ዕድገት ማፋጠን አማራጭ የለውም።
አሁንም የኪራይ ሰብሳቢነት ፖለቲካል ኢኮኖሚ በልማታዊ
አስተሳሰብ በሚፈለገው ደረጃ ባለመተካቱ የሚያጋጥሙ ችግሮችን በፅናት መታገል እንደሚያስፈልግ ኢህአዴግ በፅኑ ያምናል። የመልካም
አስተዳደርን በሚመለከት የሚነሱ ችግሮችን ለመቅረፍ ህዝቡን ባሰተፈ መልኩ ኢህአዴግና መንግስት አቅጣጫዊችን አስቀምጠው እየተረባረቡ
ይገኛሉ።
ይሁን እንጂ የሀገራችን ሁለንተናዊ ዕድገት ለማደናቀፍ የሚንቀሳቀሱ የውጭና የውስጥ ኃይሎች አሉባልታዎችንና የፈጠራ ወሬዎችን
በማሰራጨት ተገቢ ላልሆነ ርካሽ ፕሮፓጋንዳ መጠቀሚያ ለማድረግ ከልማት አጀንዳችን ለማስወጣት ሲፍጨረጨሩ ይታያሉ። ህዝባችን እነዚህን
የፀረ ሰላም እና የፀረ ልማት ኃይሎች እንደተለመደው ሁሉ በፅናት በመታገል ለሀገራችን የህዳሴ ጉዞ መሳካት የሚያደርገው ርብርብ
አጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታ።
በመጨረሻም ባለፉት 23 ዓመታት ያስመዘገብናቸውን ስኬቶች አጠናክሮ በማስቀጠል ለቀጣይ ድልና ስኬት እጅ ለእጅ ተያይዘን
የሀገራችን ህዳሴ እውን ለማድረግ የህዝባችን ተሳትፎ ከምን ጊዜውም በላይ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ኢህአዴግ ጥሪውን ያቀርባል።
ክብርና ሞገስ ለትግሉ ሰማእታት!
የኢህአዴግ ምክር ቤት ፅሕፈት ቤት
ግንቦት 19 ቀን 2006ዓ.ም
No comments:
Post a Comment