ከልጅ አኪናሆም
ይቺን አጭር ፅሁፍ ለመፃፍ ያነሳሳኝ የሰማያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር ኢንጅነር
ይልቃል ጌትነት በባለፉት ጊዜያት አቶ አንዳርጋቸው ፅጌን አስመልክቶ የሰጧቸው ማብራሪያዎች እና በኢትዮ ምህዳር የረቡዕ ሀምሌ
9 ቀን 2006 ዓ∙ም እትም ሰማያዊ ፓርቲ መሰዋዕትነት ለመክፈል መዘጋጀቱን ማስታወቃቸውን ማንበቤ እኚህ ሰው ምን ነካቸው? በማለት ብቻ ለማለፍ ባለመፈለጌ
ነው። ሰማያዊ ፓርቲ በሕጉ መሰረት ተመዝግቦ በምርጫ ቦርድ እውቅና ተሰጥቶት እየተንቀሳቀሰ እንደሆነ አውቃለሁ። በህጋዊነት መዝገብ
ላይ የሰፈረ ፓርቲ ደግሞ ህግን በተከተለ አግባብ ብቻ ተንቀሳቅሶ
ወደ ስልጣን መምጣት ያለበት ይመስለኛል፡፡ እርስዎ ግን ከዚህ በተቃራኒው ሲጓዙ ተመልክቻለሁ። በሰላማዊ መንገድ ሀሳብን
መግለፅና ብረት አንግቦ ጎራ ለይቶ መፋለም በተግባር ፍፁም የማይገናኙ ናቸው፡፡ እርስዎ ግን በሰላም ጥላ ስር ራስዎትን ወሽቀው
“አስፈላጊውን መሰዋዕትነት ለመክፈል ተዘጋጅቻለሁ” አሉን። ኢንጂነር እንደው ይህች እከፍላታለሁ ያሏት "መሰዋዕትነት"
ራስዎትን የጀግና ስም ሰጥተው ለመሸለል ባልሆነ፡፡
ምን ይሄ ብቻ በሰላማዊ መንገድ ስልጣን መረከብ እፈልጋለሁ በሚለው ፓርቲዎ
ስምም "መንግስታዊ ሽብርተኝነትን የሚሸከም ትከሻ አይኖረንም" ሲሉ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡ እኔም እኚህ ሰው የሽብርተኝነት
ትርጉሙ ተዛባባቸው እንዴ ስል እራሴን ጠይቄ ተገረምኩ። መቼም መንግስት እያደረገ ያለው ሽብርን የመከላከል ስራ ገልብጠው መንግስት
ሽብር እየነዛና ህግ እየጣሰ ነው ይህን ለመከላከልም ለትግል እየተዘጋጀን
ነው ያሉት እንደው እስኪ የቀዘቀዘው ስሜ ለጥቂት ጊዜም ቢሆን በሚዲያው ይወራጭ ብለው ባልሆነ፡፡ ኢንጂነር በመጀመሪያ ሀገሩንና
ህዝቡን የሚወድ መሪ ለግላዊ ህይወቱ ቅድሚያ አይሰጥም። በተለያዩ የአውሮፓ ሀገራት እየተዟዟሩ በተቃዋሚ ፓርቲ ስም ለሚሰበስቡት ገንዘብ ሲሉ ሌላ ፓርቲን መክሰስ፤ ማንቋሸሽ
ምን አመጣው? እርስዎና መሰሎችዎ እያወራችሁ፤ እየዛታችሁ የምትኖሩትስ ምን ሊባል ነው? ኢህአዴግን ካልተሳደቡ፣ በእውነት ላይ ሸፍጥ
ካላነሱ እና እውነታውን ሸምጥጠው ካልካዱ እርዳታና ድጋፍ አይገኝም የተባሉ ያህል ተሰማኝ።
ሀገሪቱን
የሚመራው መንግስት እኮ ህዝቦቹን የመጠበቅ ግዴታ አለበት። ዛሬ ላይ በሽብር ጥቃት እየተናጡ ያሉ ሀገራትን በመመልከት ብቻ የመንግስትን
ሚና ምን መሆን እንዳለበት ለመገንዘብ በቂ ነው። ሶማሊያ፤ ኬንያ፤ ናይጄሪያ፤ ማሊ፤ ግብፅ፤ ሊቢያ፤ ቱኒዚያና ሌሎችን ማንሳት ይቻላል።
የኢትዮጵያ መንግስት ያለውን አቅም ሁሉ በፀረ ሽብር ዘመቻው መጠቀሙ ህዝቦቹን ከስጋት ለመጠበቅ እንዳስቻለው እርስዎና መሰሎችዎ
ለመቀበል ፈቃደኛ ባትሆኑም ለበርካቶቻችን ግን ሃቅ ነው። መቼም ይሄ የኢንጅነርነት ማዕረግ እንዲሁ እንዳልሆነ ልገምት፡፡ ለነገሩ
ፖለቲከኛ ነኝ ብለው አይደል ፓርቲ እየመሩ ያሉት በእርግጠኝነት የአፍሪካን የፖለቲካ ሁኔታ ለመገንዘብ አይቸግርዎትም እኛ በሽብር
ተጋላጭነታችን ቢሆንማ ኖሮ የርካታ አስከፊ አደጋዎች ሰለባ በሆንን ነበር።
ሆኖም ኢትዮዽያዊ ሁሉ ለሽብር ድርጊትና ለፅንፈኝነት ቦታ የማይሰጥ መሆኑና
መንግስት ዜጎቹን ለመጠበቅ የሚያደርጋቸው በብቀት የተሞሉ የቅድመ መከላከል ጥረቶች ባይኖሩ ኖሮ ዛሬ ላይ መካከለኛው ምስራቅ፣ ምዕራብ
አፍሪካና ሌሎች ሀገራት ላይ ያለው የሽብር ስጋት እና እልቂት ውስጥ በገባን ነበር። አንድ ነገር መጨመር እፈልጋለሁ። አቶ አንዳርጋቸው
ፅጌን አስመልክቶ የሰጧቸው ማብራሪያዎች እሳቸው እንግሊዛዊ ሆነው
ለኢትዮዽያ ህዝብ የነፃነት ታጋይ መስለው እንዴት ሊቀርቡ ቻሉ? ኤርትራ ድረስ ሄደው ቡና ጠጥተው ተመለሱ ነው የሚሉት? የኤርትራ
መንግስት በአሁኑ ሰዓት ከኢትዮዽያ ጋር ያለው ግንኙነት እንደሆነ ፀሀይ የሞቀው ጉዳይ ነው። ምናልባት ኢንጅኔር ሌላ ስም ካልሰጡት
ማለቴን ነው። የእነ አቶ አንዳርጋቸው የቀውስ ስምት ኃላፊውና አዛዡ ኢሳያስም ቢሆኑ ሀገራችንን ሲመለከቱ የጥፋት አዕምሯቸው እረፍት
የማያገኝ፤ ሁሌም ጠፍተን ማየትን የሚፈልጉ ናቸው።
ታዲያ የአቶ አንዳርጋቸውና የፕሬዚዳንት ኢሳያስ ግንኙነት ለሀገራችን ሰላም
ሊወያዩ ነው ለማለት ምን ቀረብዎ ኢንጅነር? ባለፉት ዓመታት ያሴሩብንና ለጥቃት ያጋለጡንን መመልከት እንደማይፈልጉ በመዘንጋት እንዳልሆነ
ግን ልብ በሉ። ከዚያ ውጭ ይቺን ሀገር የመጠበቅ ግዴታ ያለበት መንግስት በሽብር ድርጊትና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ተሰማርተው በሚገኙ
ቡድኖችና ግለሰቦች ላይ ሕጋዊ እርምጃ ቢወሰድ ምንድን ነው ጥፋቱ? የእርስዎ ቅሬታስ መነሻው ምን ይሆን!? ኢትዮዽያ ለማንኛውም
አይነት የሽብር ድርጊት መናኸሪያ እንድትሆን የሚፈልጉ ሁሉ እሪታቸው ይታወቃል። በፈለጉበት ቦታ የማፈንዳት፤ ህዝቡ እየኖረ ያለውን
ሰላማዊ ህይወት የማመሰቃቀልና የራሳቸውን የፖለቲካ አጀንዳ ለማራመድ ነው። እናም ይህ ግልፅ ዕቅድ መጨናገፉ እንዴት ኢንጅነር ሊያስኮርፋቸው
ቻለ ብዬ እንዳልጠይቅ ምላሹ ግልፅ ስለሆነ ለጊዜው ልለፈው!
ኢንጅነር ይልቃል ምላሹን ከእርስዎ የማልፈልገውን አንድ ጥያቄ ልጠይቅዎ
አሁን የሰማያዊ ፓርቲ አመራር ሆነው እየተንቀሳቀሱ ነው። የመረጡት መንገድ ሰላመዊ ወይስ መሰዕዋትነትን የሚያስከፍለውን መንገድ?
ባለፉት 10 ቀናት እያስተላለፉ ያለው መልዕክት ግን ለሀገራችን የሚበጅ
ምንም ነገር የለውም፤ የማይጠበቅ ቢሆንም! እዚህ ሰላማዊ ትግል አካሂዳለሁ እዚያ ደግሞ የሚከፈለውን መሰዋዕትነት ለመክፈል ተዘጋጅተናል
ይላሉ። ወይ “መስዋዕትነት” እንዲሁ በእርስዎ መቀለጃ ከመሆኗ በፊት ለህዝብ ጥቅም ሲባል የራስን ጥቅምና ፍላጎት ላይ ሁሉም ዓይነት
ገደብ ማድረግ የሚል ግርድፍ ትርጉም ነበራት! በአንድ ሀገር ውስጥ የህግ የበላይነትን ለማረጋገጥ ተጠርጣሪዎች በሕግ ቁጥጥር ስር
ሲውሉ ግን መስዋዕትነት ብሎ ነገር አልነበረም፣ለወደፊቱም በፍፁም አይኖርም! ሆኖም መታሰራቸው ወንጀለኛነታቸውን አያረጋግጥም፣ እርስዎ
የሚሉት ነገር ከሌለ ማለቴን ነው።
መቼም እርስዎን ህጋዊ አካሄድን ለማሳወቅ የሕግ ሀሁ ማለቱ አስፈላጊ ነው
ብዬ አልወስድም። ግን እርስዎ እያነሷቸው ያሏቸው የተውገረገሩና የተምታቱ የፖለቲካ አጀንዳ የሚመስሉ እዚህም እዚያም የሚረግጡ አስተያየቶችና
አቋሞች የ21ኛ ክፍለ ዘመን ስለመሆናቸው እያጠራጠሩን ነው። እንዲህ እንደፈለጉ የሚያስፈራሩት፤ የሚዘረጥጡት፤
የሚናገሩት፤ በነፃነት የሚንቀሳቀሱባት ሀገር እኮ ይህ ፓርቲና መንግስት የሚመራት ኢትዮጵያ ናት። በተለያዩ ሚዲያዎች የሚሰጧቸውን
መግለጫዎች እከታተላለሁ፤ ሆኖም ይህን በማድረግዎ ሲጠየቁ አላየሁም፤ በነፃነት ይወጣሉ ይገባሉ። መንግስትም አሸባሪ ነዎት አላለዎትም
ምክንያቱም ሰላማዊውን መንገድ መርጠው እስከተንቀሳቀሱና ከሽብር ድርጊት እስከራቁ ድረስ ማለቴ ነው። ይህ ስል ካልተሳሳትኩኝ ማለቴ
ነው ኢንጅነር! ግን እርስዎ የሀምሌ 9 ቀን 2006 ዓ∙ም መግለጫዎና
አቶ አንዳርጋቸው ፅጌን አስመልክቶ የሰጧቸው የተንሿረሩና ላይና ታች የሚረግጡ “ትንታኔዎች” ወይ ኢንጅነር ምን ነካቸው እንዲል
አስገድስደውኛል!
በመግለጫ”ዎ” ሀገራችንንም ህዝባዊ በአምባገነን ስርዓት ከምትመራው ኤርትራ
ጋር አነፃፅረው መግለጫ ማውጣትዎን አንብቤያለሁ፤ትዝብት ላይ መጣሌንም አልሸሽግም። በእርግጥ በስልጣን ላይ ያለው መንግስት እርስዎን
መሰል ተቃዋሚ እንዳለው ሁሉ በርካታ ደጋፊዎች ያሉት ድርጅት ስራውን በተግባር እያሳየ ያለ መሆኑን በሌላ ነገር ተሸብበው ካልሆነ
ይጠፋብዎታል ብዬ አልገምትም። ምክንያቱም በዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ ዘንድ የሀገራችን ለውጥ ተገቢውን እውቅና እየተቸረው ነውና!
ለንፅፅር የማይበቃ ተራ ነገርን ከሀገራችን ፈጣን፣ ተከታታይና ፍትሐዊ ዕድገት እንዲሁም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጎለበተ ካለው የዴሞክራሲ
ስርዓታችን ጋር ማነፃፀር የሚጠበቀው ከማን እንደሆነ ጠፍቶኝ ግን አይደለም!
ከምንም በላይ ደግሞ ህዝቡ ይወክለኛል ላለው የፖለቲካ ፓርቲ ማለትም ኢህአዴግ
በአደባባይ ድምፁን ሰጥቶት ኢህአዴግም የተሰጠውን አደራ ለመወጣት ቀን ተሌሊት እየተጋ ባለበት ወቅት እን ኢንጅነር እና መሰሎችዎ
ትወጡና ባልተሰጥዎት ስልጣን “ስለህዝባችን” እያላችሁ ውስጣዊ ማንነታችሁ ታሳዩናላችሁ! በመቀጠልም ያለገደብ በማውገርገር ህዝቡን
ለማደናገር በማለም ህዝቡ እንዲሰራለት የመረጠውን ድርጅት ተልዕኮውን እንዳይወጣ እናንተ ራሳችሁ ስራ ትሆናላችሁ! ወይ መቃወም!!
ኢንጅነር አልተመረጡም ማለት ኢህአዴግ አልተመረጠም ብሎ መደምደም ሀገርን
እመራለሁ ብሎ ዝግጅት እያደረገ ካለ የተቃዋሚ ፓርቲ የሚጠበቅ አይመስለኝም። ኢህአዴግን ለመፎካከር አቅሙና ሞራሉ ሰማይ እንደሆንብዎ
በውል ስለሚገነዘቡም ቀድመው ጥላሸት በመቀባት ወደ ፊት በመራመድ ለሀገሩና ለህዝቦቹ እየሰራ ያለን ድርጅት መንቀፉን ይመርጣ፣ ይዝታሉ፣
ይነቅፋሉ፤ ይዝታሉ፣ ይፎክራሉ ብቻ ብዙ ብዙ ነገር ይላሉ። ዴሞክራሲ ማለት የህዝቡን ጥቅም ለማረጋገጥ እንጂ የግለ ሰዎች ፍላጎት
እና የቀን ሕልም ለማሳካት የሚዘጋጅ በሰው ልክ የሚሰፋ ቀሚስ መሆን አይችልም! ሰዎች ሀሳባቸውን የመግለፅ፤ስሜታቸውን የማንፀባረቅ፤
ይሁን እንጂ ሀገራችን በዴሞክራሲያዊ ባህሏ ዳብራ አድጋና ተመንድጋ ለማየት ጭፍን ተቃዋሚዎችና ጭፍን ደጋፊዎች መስመር ሊይዙ ይገባል።
በምክንያት የሚያምን፤ በምክንያት የሚቃወምና የሚደግፍ ፓርቲ ያስፈልጋል። እናንተ ስለ ሀገራችን ከምታውቁት በላይ ህዝባችን በዝርዝር
ያውቃል። እንዲያውም የሀገራችን ህዝቦች ግራ ቀኙን ማመዛዘን የሚችሉ በመሆናቸው እንጂ እርስዎን መሰል “የፖለቲካ መሪዎች” የሚያጨልሟት
ኢትዮዽያን ባናውቅ ኖሮ ተጨራርሰንና ተላልቀን ነበር። ይህን ሁሉ የተንሿረረና የተዛባ መረጃ እየሰጣችሁት ጆሮ ነፍጓችሁ ሰላሙንና
ልማቱን የመረጠውን የሀገሬን ህዝብ እያየሁ እደመማለሁ። ግልብ የፖለቲካ መሪዎች ከግራና ከቀኝ በሚያላትሙት ተራ ወሬ ቢሆን ኖሮ
ኢትዮዽያ ዛሬ አትኖርም።
አሁንም ግን ኢንጅነር ቆም ብሎ በማሰብ ሽብርተኝነትንና የሽብርተኝነት
ድርጊትን ከሰላማዊ ትግል ለመለየት ጊዜው ያንሳል የሚል እምነት የለኝም። እናንተ ግራ ተጋብታችሁ እኛንም ግራ አታጋቡን። በተለያዩ
ሚዲያዎች የምትሰጧቸው “መግለጫዎች” እኮ ህዝብን ያደናግራሉ። እንዴት ነው የተምታታ እና የተውገረገረ “መግለጫ” እየሰጣችሁ አመኔታ
የሚኖረን? ጥሩውን ጥሩ፤ መጥፎውን መጥፎ የሚል ግልፅ አቋም ሳይኖራችሁ ሀገርና ህዝብ ስለማስተዳደር ትነግሩናላችሁ። እናም ኢንጅነር
ጣትዎን ወደ ውጭ ከመቀሰርዎ በፊት ራስዎን በመመርመር መራመድ ይገባዎታል እላለሁ። በሰላም ሀገር ኡኡታ፤በተረጋጋ ህዝብ መካከል
ሽብር እየፈጠሩ ያሉት እርስዎ እንጂ መንግስት አይደለም። ሰማያዊ ፓርቲ “መሰዋዕትነት” ለመከፈል መዘጋጀቱንም ነግረውናል። እስከ ምን ድረስ ነው? ኢሳትን እንደሚጠቀሙም አውጀዋል። መጠቀም ከጀመሩ
እኮ ሰነባብተዋል፤ በርካታ ማብራሪያዎችን ለኢሳት እየሰጡ እንደነበረም እከታተላለሁ። ታዲያ ዛሬ ምን አዲስ ነገር ተፈጠረና ነው
ኢሳትን እንደሚጠቀሙ አዋጅ መንገር ያስፈለገዎ? ልብ ማለት ያለብዎት ነገር ደግሞ ግንቦት ሰባት ሀገራችን የሽብር ድርጊት ከሚፈፅሙ
ዝርዝር ውስጥ ከተካተተ ሰነባብቷል። ኢሳት ደግሞ የግንቦት ሰባት ልሳን ነው። ታዲያ ኢሳትን መጠቀም ከግንቦት ሰባት ጋር ውህደት
መፍጠርዎ ይሆን? ወይስ ሌላ አጀንዳ ማንሳት ፈልገው? አበቃሁ
No comments:
Post a Comment