ልጅ አኪናሆም
በአለማችን የሚዲያ እድገት በርካታ ምዕተ አመታትን እንዳስቆጠረ የየጊዜው
በዘርፉ የተሰናዱ ድርሳናት ያትታሉ። ዛሬ ላይ ሁላችንም ሚዲያ የሚለውን ቃል የእለት ከእለት መግባቢያ ቃል አድርገን እየተጠቀምንበት ሲሆን የቃሉ መሰረት ”neuter of medius
(middele)″ ከሚል የላቲን ቃል የተገኘ ሆኖ የተለያዩ የማስ ኮሙዩንኬሽን ማስተላለፊያ ዘዴዎችን ለመግለፅ የምንጠቀምበት እንደሆነ
ብዙዎቻችንን ያግባባል። ቴክኒካዊ ትርጉሙም ከማንም ጋር ያልወገነና አንድን መልዕክት ከላኪ ወደ ተቀባይ በብቃት ለማድረስ የሚችል
አገናኝ መሳሪያ ማለት ይሆናል። በሌላ አገላለፅ ሚዲያ መረጃን ለማሰባሰብ፣ ለማደራጀትና ለማሰራጨት አገልግሎት ላይ የሚውል በአብዛኛው
ጊዜ ከማስ ሚዲያ ጋር ተመሳሳይ ትርጓሜ የሚሰጠው የመገናኛ ዘዴ ነው። ሚዲያ ህብረተሰቡን ለሀገራዊ ግንባታና ለለውጥ የሚያነሳሱና
ህዝቡን የሚጠቅሙ መረጃዎችና መልዕክቶችን በብቃት ማስተላለፍ ያስችላል። እናም ሚዲያ በአንድ ሀገር ፖለቲካዊ፤ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ
እንቅስቃሴ ውስጥ ወሳኝ ሚና ከሚጫወቱ ተቋማት መካከል አንዱ ነው።
በሚዲያ እድገት ውስጥ ቀዳሚ ተጠቃሽ የሚሆነው የህትመት ኢንዱስትሪው ሲሆን
ከ15ኛው እስከ 17ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ባለው ጊዜ እንደተጀመረ የታሪክ መዛግብት ያትታሉ። በነዚህ ጊዜያት የህትመት ስራ አነስተኛ
ኢንዱስትሪ የነበረ ቢሆንም ጋዜጦች በነበራቸው ተቀባይነት ሲመዘን የፕሬስ ስራ ኢንዱስትሪውን እስከ መምራት የደረሰበት ወቅት እንደነበረም
መረጃዎች ያመላክታሉ። በነዚህ ጊዜያት የግለሰቦች የማተም መብት እስከምን ድረስ ሊሆን ይገባዋል የሚለው ብዙ ሲያከራክራቸው ነበር።
አንድ አይነት አመለካከት ያላቸው የህብረተሰብ ክፍሎች (የእምነት ተቋማት) አባሎቻቸው የሚያወጧቸውን ህትመቶች ለመቆጣጠር ያላቸው
መብት እስከ ምን ድረስ ነው? የተለያየ እምነት ከሚያራምዱትስ ጋር ተቻችሎ እንዴት መኖር ይቻላል? የአታሚዎች የህትመት ፈቃድና
በሚያትሟቸው ጉዳዮች ላይ ያላቸው ተጠያቂነት ምን ይሆናል? ሳንሱርን ወይም ሌላ የቁጥጥር ዘዴን እንዴት ማከናወን ይቻላል?ወዘተ
የሚሉ ጥያቄዎች በስፋት ይነሱ ነበር። በነዚህ ጉዳዮች ላይ የሚካሄዱ ክርክሮችም የጋራ መግባባት የተያዘባቸው ባለመሆናቸው በወቅቱ
የነበረው ″የኮሙዩኒኬሽን ጦርነት” ተብሎ እስከመጠራትና በህብረተሰቡ ውስጥም የመቻቻል ባህል እየጠፋ የሄደበት ሁኔታ እንደነበር
ይጠቀሳል።
በዘመኑ የነበሩ አውሮፓውያን ነገስታት በአደባባይ የሚታተሙ ግብረ ገብነት
የጎደላቸው ሀሳቦችን የመቆጣጠር መንግስታዊ ግዴታ አለብን በማለት ሳንሱር የጀመሩበት ወቅትም ነበረ። እናም በቀደምት ዘመናት በአንድ በኩል የልቅ ነፃነት የሚዲያ ፍልስፍና መሰረት የጣለበት፤ በሌላ በኩል
ደግሞ ነፃነትና መቻቻል እየጠፋ እንዳይሄድ ከባድ ፈተና የተደቀነበት የማስ ሚዲያ የእድገት ዘመን እንደነበረ ይታወሳል። ከአንደኛው
የአለም ጦርነት በኋላ የኮሙዩኒኬሽን ቴክኖሎጂ በከፍተኛ ሁኔታ ተስፋፍቷል፤ አዳዲስ የሚዲያ አውታሮች ተፈጥረዋል። ይህ ሁኔታ በህዝብ
ሚዲያ አስፈላጊነት፤ አመራርና ቁጥጥር ላይ የራሱን ተፅዕኖ እያሳደረ መጥቷል። በተለይ በ20ኛው ክፍለ ዘመን አጋማሽ ላይ በአንድ
በኩል ሚዲያ ትርፍን ለማጋበስ ሲል በስሜታዊ አቀራረብ ህዝቡን ያማረረበት፤በሌላ በኩል ደግሞ መንግስታት ሚዲያውን የመቆጣጠርና የመግዛት
ፍላጎት ያሳዩበት ሁኔታ ታይቷል። ሚዲያውን አስመልክቶ በተለያዩ ዘመናት አከራካሪ ጉዳዮች እየተነሱ ያለፉ ቢሆንም ሚዲያው ለህዝብ
የሚጠቅም ስራን ማከናወን አለበት የሚለው ግን በተለያዩ ጎራ ተከፍለው በሚነሱ ፍልስፍናዎች ላይ እንኳ ወደ መግባባት አምጥቷል።
ወደ ሀገራችን ሚዲያዎች በተለይ የህትመት ሚዲያዎች ስንመጣ በአብዛኛው የግል
የህትመት ውጤቶች ወደ ኋለኛው ዘመን የአውሮፖውያን መንገድ ተመልሰው እየሰሩ በመሆናቸው ለአንድ ሀገር ልማት አስተዋፆ ከማበርከት
ይልቅ ልዩነትን በማስፋትና መቻቻልን በማጥፋት ላይ አተኩረው በመስራት ላይ መሆናቸው ለኛ ኢትዮዽያውያን ግልፅ ነው። እኔም በመግቢያዬ
ስለ ሚዲያ ታሪካዊ አመጣጥና የነበሩትን ተግዳሮቶች ለመዳሰስ መሞከሬ የሀገራችንን ነባራዊ ሁኔታ ለማየት ይረዳን እንደሆነ በሚል
ነው።
ሚዲያ ዘርፈ ብዙ ጥቅሞች እንዳሉት የሚያጠያይቅ አይደለም። ምክንያቱም እውነታው
የህትመት ሚዲያው በተአማኒነት ላይ የሚያተኩር፤ የዘመኑን የስልጣኔ ደረጃ መዝግበው ለትውልድ የሚተላለፍ ብቃት ያላቸውና መረጃዎቹን
እንደማጣቀሻ ለማንበብ የሚያስችሉ ህያው መማሪያ መፃህፍት መሆናቸው ሲሆን በአሁኑ ወቅት በሀገራችን እየታተሙ ያሉ የጋዜጣና የመፅሄት
ውጤቶች ግን አብዛኞቹ ሙያዊ ኃላፊነታቸው በአግባቡ እየተወጡ እንዳልሆኑ እርዳለሁ። እዚህ ላይ ለማሳያነት ይሆን ዘንድ በቅርብ ጊዜ
የታተሙ ጋዜጦችና መፅሄቶች ይዘው ያወጧቸውን ርዕሰ ጉዳዮች በጥቂቱ እንመልከት። እዚህ ላይ ማሳየት የሚፈልገው የግል ምልከታዬን
ነው። ምክንያቴ ሀገር የምትለወጠው ሽብር በመንዛት፤ በበሬ ወለደ
ዓይነት መረጃ ህብረተሰቡን በማወናበድና ትንሽ እውነት ይዞ በሀሰት ወሬ ለውሶ እና መርዞ ማቅረብ እጅግ አሳዛኝና ከስነ ምግባር
ያፈነገጠ፤ ውጤቱ ደግሞ በቀጣይ ትውልድ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ የሚያሳድር ከመሆን ባለፈ የሚጠቅመው አንዳችም አይነት መልካም ነገር
አለ ብዬ ስለማላምን ነው።
በየሳምንቱ የሚታተሙ በርካታ የህትመት ውጤቶችን ለማንበብ ጋዜጦችና መፅሄት
ተራ መሰለፍ ግድ ያለኝ ባይሆንም መረጃ ለማግኘት ገዝቼም ሆነ ሳንቲሞችን ከፍዬ የማነባቸው የህትመት ውጤቶች በውስጤ ያለውን መልካም
ነገር ከመሸርሸራቸውም ባሻገር አጠገቤ ያለውን ሰው የማላምን፥ ሁልጊዜም በፍርሃትና በጭንቀት የተሞላሁና ጨለምተኛ አካሄድን እንድከተል
ያደረጉኝ እነዚህ ፅንፍ የያዙ የተወሰኑ የግል ይህትመት ውጤቶች ናቸው ብዬ እንዳምን ተገድጃለሁ። እዚህ ላይ አንባቢዎቼ እንድትረዱኝ
የምፈልገው ነገር አንዳንድ ፀሃፊያን እንደነዚህ አይነት እጅግ በጣም የተጋነኑ፥ የበሬ ወለደ ዓይነት፥ ጨለምተኛነት የሚታይባቸውና
በሀገር አንድነት ላይ አሉታዊ አቀራረብ የሚያመዝንባቸው ፅሁፎችን በተደጋጋሚ ለህትመት ሲያበቁ ተመልክቻለሁ። ይህን የሚያደርጉት
ለምንድን ነው ብዩ መጠየቄ አልቀረም። አንዳንድ ፀሃፊያን እነዚህ መሰሎችን ፅሁፎች ካነበቡ በኋላ ስህተት መሆናቸውን ለማሳየትና
ሚዛናዊ ዘገባ ሲሰሩና እንዲሰሩ ሲጠይቋቸውም የገዥው ፓርቲ ተለጣፊዎች፥ አሸርጋጆች፥ ለሆዳቸው ያደሩ ሆዳሞች፥ አዕምሮ የሌላቸውና
ሌላም ሌላም ስነ-ምግባር የጎደላቸው ተራ የስድብ መዓቶች በማዝነብ የማሸማቀቅ ስራ ሲሰሩ ተመልክቼ ታዝቤያለሁ።
እነዚህ የሕትመት ውጤቶች ሁሉም ሰው ገዥው ፓርቲን እንዲጠላና እያከናወነ
ያለውን ዘርፈ ብዙ መልካም ተግባራት ጥላሸት በመቀባት ብሎም በማህበረሰቡ ዘንድ ሚዛናዊነት የጎደለው አስተሳሰብና ድርጊት እንዲሰርፅና
የተደበቀ አጀንዳቸውን በተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች ስም በርካታ አስፀያፊ ተግባራትን እያከናወኑ እንደሆነም አምናለሁ። በየትኛውም
ዴሞክራሲያዊ ሀገር እንደሚደረገው ሁሉ የሀገራችን መንግስት ህጎች ተጥሰው ሲገኙ የህዝቦች ጥቅምና ፍላጎት ለመጠበቅ ሲባል አስፈላጊውን
ህጋዊ እርምጃ የመውሰድና የህግ የበላይነትን የማረጋገጥ ግዴታ አለበት። ደግሞም በየትኛውም ሀገር ሁሉም ሰው በሁሉም አስተሳሰቦች
አንድ ዓይነት ይሆናል፣ የአስተሳሰብ ልዩት ማጥፋት ይቻላል ብሎ ማሰብ ምክንያታዊ እይታ ሊሆን አይችልም። የፍላጎት ልዩነት አለመጣጣም አይደለም በሀገርና በህዝቦች መካከል በቤተሰቦቻችን
ደረጃም ልዩነት አለ። ይህ ልዩነትም በአግባቡ ካልተያዘ ወደ ግጭት ሊያመራ ይችላል
የኢፌዴሪ መንግስት እነዚህን የፍላጎትና የኑሮ ልዩነቶችን ለማጥበን እንዲሁም
ለማጣጣም እየሰራ ቢሆንም እነዚህ ጨለምተኛ ፅሁፎች ግን በየጊዜው ዳንቃራ ሲሆኑ እታዘባለሁ። የእነዚህ ጨለምተኛ የሕትመት ውጤቶች
የስርጭት አድማሳቸው እጅግ ጠባብ እና በአዲስ አባበና በአዲስ አበባ ዙሪያ የታጠሩ የፕያሳ ወሬዎች ስለሆኑ ተዕእኖ የኘኛሳደር አቅማቸው
እዚህ ግባ የሚባል ቢሆንም! የተፅዕኖ ደረጃቸው ከራሳቸው እና መሰሎቻቸው
የዘለለ ባይሆንም ቅሉ ነጋ ጠባ የሚሰብኩት ግን ሁከትና ብጥብጥን፣ አለመረጋጋትና መናጋትን፣ አለመቻቻልና መናቆርን በመሆኑ በእውነትም
የጥፋት መልእክተኞች ናቸው ለማለት እገደዳለሁ! እስኪ የትኞቹ ፅሁፎች ናቸው በሀገር ግንባታና በህዝብ ፍላጎት ላይ ጊዜያቸውን የሚያጠፉት?
መልሱ እጅግ በጣም ጥቂት የሆኑ ኃላፊነት የሚሰማቸው ብቻ ብሎ ማለፉ ሳይሻል አይቀርም!
በህዝባችን መካከል ድሮም የሃይማኖት ልዩነት ነበር፤ ድሮም የብሄረሰቦች ልዩነት
ነበር፤ ድሮም የወንዜ ልጅ መባበልና የአካባቢን ሰው ከሌላው የማቅረብ ሁኔታዎች ይስተዋሉ ነበር፤ ድሮም የአስተሳሰብና የአኗኗር
ዘይቤ ልዩነቶች ነበሩ። ልዩነቱ ዛሬ ላይ እንዲህ እንደፈለጉ ለህዝብ ጆሮ ለማድረስ አስፈላጊ የማትሆነውን ጉዳይ ይዞ በፊት ገፆች
ላይ ሮጦ መለጠፍ የሚያጣድፍ ጉዳይ ከብሔራዊ ጥቅም ይልቅ ለግል እኩይ ፍላጎት የማዋል ሁኔታ ከየት መነጨ ብዬ ለመጠየቅም ተገደደኩኝ-መልሱ
በጣም ግልፅ ቢሆንም! እነዚህ የግል የሕተመት ውጤቶች ሕገ መንግስታዊ
መብቶቻቸውን አለአግባብ በመጠቀም ከሙያዊ ስነ-ምግባር ባፈነገጠ ሁኔታ ለግል አልያም ለቡድን ፖለቲካዊ አጀንዳ መሳሪያነት እየተገለገሉበት
እንደሆነም ለሁላችን ግልፅ እየሆነ መጥቷል። እንጂ ልዩነታችን እማ
ጥንትም የኖረ፣ አሁን ያለ ለወደፊትም አብሮን የሚቀጥል ተፈጥሮአዊ ማንነታችን ነው።
ዛሬ ላይ የፕሬስ ነፃነት በመረጋገጡ እጅግ በርካታ የህትመት ውጤት የሆኑ
መፃህፍት፥ መፅሄትና ጋዜጦች ከህዝብ ጋር ተዋውቀዋል። ከነዚህ መካከል ጥቂቶቹ ወጣ ያሉና ይዘታቸውም ለአንባቢያን የማይመጥኑ በሚል
የፈረጅኳቸው አሉ። በነዚህ ጫፍ የወጡ የህትመት ውጤቶች አማካኝነትም
ግለሰቦችን ያለ አግባብ እና ኢጠሞራላዊ በሆነ አኳኋን የሚዘለፉባት ሀገር ኢትዮዽያ ሆናለች (እነዚህ የሕትመት ውጤቶች
ከአዲስ አበባ የመውጣት ዓቅማቸውም ሆነ ፍላጎታቸው በእጅጉ የታጠረ ቢሆንም)፤ እንደፈለጉ ስሜታቸውን እንጂ የህዝብን ፍላጎትና መንገድ
መከተል የቀረባት ሀገር ኢትዮዽያ ብቻ ናት ለማለትም እገደዳለሁ።
እዲህ ያለገደብ እና ከሙያዊ ስነ-ምግባር ባፈነገጠ መልኩ እየተፃፈም ደግሞ
ሃይ ባይ ሲመጣ በግል ብዕራቸው ያለእነሱ አዋቂ፤ ያለ እነሱ ፀሃፊ፤ ያለ እነሱ ታላቅ፤ ያለ የማይመስላቸው በግላቸው የሲኒ ማዕበል
ውስጥ የሚናወጡ ግልቦች የእነሱን የነተበ ማንነት በነፃ ማንነታችን ላይ መጫናቸውን ቀጥለዋል። የሚያጠናቅሯቸው ፅሁፎችም በትርጉም
ከተራ ልመና ያልዘለሉ (ከገንዘብ ማስገኛነት የማያልፉ) እውቀት የማያስጨብጡ ግራ የሚያጋቡና ለዜጋው ሰላም ማጣትና ስጋት የሚሆኑ
ናቸው። አጀንዳቸውም ተደጋጋሚ፤ ወደ ፊት ፈቅ የማይል፤ የጋዜጠኝነት ስነ ምግባርን ያልተከተለ፤ አስልቺና አንዳንዴም በስድብ ስልጠናን
የወሰዱ በሚመስሉ ለማጅ ፀሃፊያን እንደተፃፉ ይታወቃል። አንደኛውን ብሄር ከሌላኛው ለማራራቅ፤ አንደኛውን የፖለቲካ ፓርቲ ከሌላኛው
ጋር ሆድና ጀርባ በማድረግ፤ አንደኛው እምነት በሌላኛው እንዲነሳ መብቱ የተነፈገ፥ መድሎ የተፈፀመበት በማስመሰል ብዙ ተብሏል።
እርግጥ ነው ፕሬሶችን አምኖ ያሉትን በሙሉ ተቀብሎ ለነውጥና ለሽብር የሚነሳሳ
ዜጋ የለም ባይባልም አብዛኞቹ የሀገራችን ህዝቦች ቀኝና ግራቸውን ማመዛዘን የሚችሉ በመሆናቸው የነውጥና የአመፅ ፀሀፊያን ሚዛናቸው
ምን ላይ እነደሆነ በህዝባችን ዘንድ ታውቋል። እኔም ለበርካታ አመታት ትክክል መስሎ ይሰማኝ ከነበረው ከጥፋት ወሬ ናዳችሁ አሁን ተላቅቄ በተረጋጋ መነፈስ መራመድ ጀምሬያለሁ። የዛኔ የህትመት ውጤቶቻችሁን
አንብቤ ወደ ቤቴ ለመሄድ ስነሳ በየመንገዱ፥ በየጥጋጥጉ፥ በየመስጊዱና
በየአብያተክርስቲያናቱ ሰው የሚጠፋፋና የሚተላለቅ ስለሚመስለኝ በፍርሃት ቤቴ የምገባባቸው ቀናት እጅግ በርካታ ነበሩ። እኔ ይህን ያህል ከሆንኩ ሌሎች እንደሚኖሩ
አልጠራጠርም። ስለ ሰላም መስበክ ህመም የሆነባችሁ፣ስለ ልማት መዘገብ ሽንፈት መስሎ የሚታያችሁ፤ ስለ መቻቻልና የህዝቦች አንድነት
ማመላከት ውርደት እንደሚሆንባችሁ ተገንዝቤያለሁ። በእርግጥ በርካታ ፀሀፊያንና አምደኞች ስለሀገራቸውና ህዝባቸው ተቆርቋሪዎች የህትመት
ውጤቶቻቸውም ሚዛናዊና አስተማሪ ብሎም መረጃ የሚሰጡ እንዳሉ በተለያዩ ጊዜያት አንብቤያለሁ።
በዚያን ጊዜ በህትመት ፈቃድና በሚያትሟቸው ጉዳዮች ላይ መግባባት ላይ ባለመደረሱ
የኮሙኒኬሽን ጦርነት ተከፍቶ በማህበረሰቡ ውስጥም የመቻቻል ባህል ጠፍቶ እንደነበር እንገነዘባለን። በአደባባይ የሚታተሙ ግብረ ገብነት
የጎደላቸው ሀሳቦች በየጊዜው ይሰነዘሩ የነበረበት ወቅት በመሆኑም በህዝቦች መካከል መተማመንና የጋራ አብሮነት መንፈስ እንዳይኖር
ከማድረጉም በላይ በርካታ የጦርነት ቀውሶች ውስጥ ገብተው ይዳክሩ የነበረውም አንዱ ምክንያት ሚዲያው የሚያሰራጫቸው መረጃዎች በህዝቡ
ዘንድ ቅራኔን እየፈጠሩ በመምጣታቸው ነበር። ታዲያ እነዚያ ሀገራት ካካሄዷቸው ተደጋጋሚ ጦርነቶች ተምረው ሀገራቸውን በእድገት ጎዳና
የማስጓዙን መንገድ መርጠዋል። ሆኖም አሁንም ድረስ ከሀገራቸው ውጭ ከየትኛውም አካባቢ የሚያጋጥሙ ሁነቶችንና ችግሮችን በአሉታዊ
አቅጣጫ በመምረጥና በማስተጋባት አሉታዊ ነገር ማቅረብን እንደ ግብ መውሰድ አላቆሙም። ችግሮችን በማጋነንና የህዝብ ስሜት የሚኮረኩሩ ዘገባዎችን በማቅረብ ጊዜያዊ ተደማጭነት ማትረፍ ችለዋል።
እዚህ ላይ ልብ ልንለው የሚገባው ጉዳይ እነዚህ የሰለጠኑ ሀገራት ሚዲያዎች
ምንም እንኳ ጊዜያዊ ተደማጭነት ቢኖራቸውም የሚያቀርቧቸው ዜናዎች ዳፋ ግን በታዳጊ ሀገራት ላይ በአሉታዊ ጎኑ የሚታይ ሆኖ እናገኘዋለን።
ምክንያቱም እነዚህ ሚዲያዎች ከእነሱ ውጭ ያሉ ህዝቦች ሁሌም በጦርነትና በድህነት አረንቋ ውስጥ ተዘፍቀው እንዲኖሩና ሁኔታዎች እንዲባባሱ
በጎደሏቸውና በችግሮቻቸው ላይ አተኩረው በመስራት ያሳጧቸዋል፤ በህዝቦቻቸውም የመነጠልና የነውጥ ስራዎች እንዲባባሱ ያደርጋሉ። እውነታው
ግን በነዚህ ሀገራት በርካታ የተለወጡና መልካም ስራዎች ሳይኖሩ ቀርተው አይደለም። በሀገራችን ውስጥም ሆነ በሌሎች ታዳጊ ሀገራት
ውስጥ ሆነው ስለእኛ የሚዘግቡት የሀገራችን ሚዲያዎችም ከነዚህ ሀገራት የቀዱትን አቀራረብ ተቀብለው በመቀጠላቸውና ሚዲያውን ከልማትና
ከሀገራዊ አንድነት ይልቅ ለግጭት ሁነቶች ትኩረት በመስጠታቸው በሀገራችን ልማት ላይ ምንም አይነት አስተዋፆ እያበረከቱ አይደለም
የሚል ምልከታ አለኝ።
ከዚህ ቀጥሎ ርዕሶቻቸውን በግርድፉ የማነሳቸው የህትመት ውጤቶች ይዘታቸው እጅግ በተንሿረረና በተጣመመ የአፃፃፍ ስልት የተፃፉ አንባብያንን
ከማደናገር ያለፈ ትክክለኛ መረጃ ያልሰጡ ግን ደግሞ በሚከናወኑ የልማት ስራዎች ላይ ጥላሸት የሚቀቡ በህዝቦች መካከልም ቅራኔና
መራራቅ የሚፈጥሩ ሆነው አግኝቻቸዋለሁና እናንተም ትዝብታችሁን አክሉበት ብያለሁ። የፌደራል ስርዓታችን ኢትዮዽያዊነትን እያጠፋ ነው፤ ዩኒቨርሲቲዎቻችን የእውቀት ሳይሆን የካድሬ መመልመያ እየሆኑ ነው፤በልማት ስም የምትዘረፍ ሀገር፤
የመሪዎች ግፍ በዝቷል የህዝቡ ብሶት ንሯል ወደ አይቀሬው እየተጓዝን ንው?፤ ኢህአዴግ እስከመቼ፤ እነ አቡበክርን በካቴና ማሰር
የኢትዮዽያን እስልምና ከማሰር አይለይም፤ በመንደር ማሰባሰብ ስም ነዋሪዎች እየተፈናቀሉ ነው፤ የኢንቨስተሮች የመሬት ወረራ ተባብሶ
ቀጥሏል፤ የፌደራል ስርዓቱ ከብተና አዳነን ወይስ ለብተና እያዘጋጀን ነው?፤ ፈንድቶ የታመቀው አብዮት፤ ምሁራኑ ስልጣኝ ሹመኞች
አሰልጣኝ የሆኑበት ዩኒቨርሲቲ ሆኗል፤ የፕሬስ ነፃነት በዴሞክራቲክ ዴቨሎፕመንታል መንግስት ድባብ ውስጥ ነው፤ የሙስሊሞች ጉዳይ
ከእሳት ወደ ረመጥ፤ ግንቦት 20 የወለደው የመለያየት አደጋ፤ ግንቦት 20 አንድን ፈላጭ ቆራጭ በሌላ ፈላጭ ቆራጭ አገዛዝ ነው
የተካው፥ ኢህአዴግ የመለሰው አንድም ጥያቄ የለም፥ የሚሉና ሌሎች እጅግ በርካታ በአሉታና በተዛባ መልኩ የታተሙና የተዘገቡ ጉዳዮችን
ማንሳት ይቻላል።
እኔ እንደተረዳሁትና እንደገባኝ እንደዚህ ለማፃፍ፥ ለመዝለፍና የፈለጉትን
ለማለት ያስቻላቸው ባለፉት ዓመታት መንግስት ለፕሬስ ነፃነት በሰጠው ህገ መንግስታዊ ዋስትና የተረጋገጡና የመጡ ናቸው። ይህን እውነታ እውቅና ከመስጠትና ከማበረታታት
ይልቅ ተቃርኖ ይቀድማቸዋል። በሀገሪቱ ጉዳዮች ያለገደብ መፃፍ የተቻለው በኢህአዴግ የሚመራው የኢፌዴሪ መንግስት ባረጋገጠው ነፃነት
ነው። ግን ሁሌም ህግ የማይገዛቸውና እንደልባቸው የሚፅፉ አካላት በተቃርኖ በመቆም የተሰጠው እንዳልተሰጠ፥ የተደረገው እንዳልተደረገ፥
የሆነው እንዳልሆነ፥ የተመዘገበው ልማት እንዳልመጣ፥ የተረጋገጠው የሀይማኖትና የህዝቦች እኩልነት እንዳልመጣ አድርገው ያቀርባሉ፤
ይዘግባሉ። ለልማት ቀናኢነት ቢኖራቸውማ ኖሮ፤ ሀገርንና ህዝብን ቢወዱማ ኖሮ የሚከሰቱ ችግሮችን በሚዛናዊነት በማቅረብ፤ የችግሮችን
ምንጭ በመተንተንና የመፍትሄ አቅጣጫዎችን በማመላከት ህዝቡ የነዚህ ችግሮች የመፍትሄ
አካል እንዲሆን የሚያደርግ አዎንታዊ ሚዲያ መሆን ይችሉ ነበር።
ይህም ማለት የሚያጋጥሙ ችግሮችን በማራገብ “ተነባበቢ” ለመሆን ከመስራት
ይልቅ በማንኛውም ደረጃ የሚከሰቱ ችግሮችን ትክክለኛ ገፅታና የችግሮችን
ምንጭ በመተንተን የመፍትሄ ሀሳቦችን በማቅረብ ህዝቡንም ለመፍትሄው ተሳታፊ ለማድረግ መስራትና አቅጣጫ ማመላከት ይቻል ነበር። እውነታው
ግን ከዚህ በእጅጉ የተለየ ሆኖ እናገኘዋለን። በሀገራችን እጅግ በርካታ የልማት ስራዎች እየተሰሩ እያለና እነዚህን በሚገባ በመዘገብ
መረጃውን ለህዝቡ በማድረስ መስራት የሚያስችል ምቹ ሁኔታ ተፈጥሮ እያለ ሁሉም ነገር በተቃርኖና በጥፋት የሚቆሙ የህትመት
ሚዲያዎች ቁጥራቸው ቀላል አይደለም።
በየጊዜው የምዕራቡ አለም የነተበ ቲዮሪ ጋር ተቆራኝተው የሀገራችንን ብሩህ
ዘመን ለማዳመን ይታትራሉ። ለሀገርና ለህዝብ ብልፅግና መባተል ክብርና ሞገስ ያለው ተግባር ነው፤ ውሳኔንና ቀናነትን ይጠይቃል፤ የተጣመመውን ለማቅናት፤ የቆሸሸውን
ለማፅዳት፤ ኋላ የቀረውን ወደ ፊት ለማምጣት፤ የተጓደለውን ለማሟላት ሚዲያ ወሳኝ መሳሪያ እንደሆነ አምናለሁ። በየሳምንቱ እየታተሙ
ከሚወጡ የተዛቡ፤ የተንሻፈፉና ህዝብን በሽብርና በፍርሃት እንዲኖር ከሚያደርጉ ሚዲያዎች ግን ምንም ባይኖር እመርጣለሁ። ቁም ነገር
ለመገብየት፥ እውቀት ለመቅሰም መፅሀፍቶችንና ጋዜጦችን ለመግዛት ወጥቼ ስመለስ ጤናማው አዕምሮዮ ተቀይሮ፥ የምራመድበት መንገድን
በፍርሃት እየቃኘሁ ቤቴ የምገባባቸው ቀናት ቀላል አይደሉም። ሆኖም በፅሁፎቻቸው እንዳሉት ሀገሬን አላገኛትም፤ ህዝቡ በሰላም ወጥቶ
በሰላም ይገባል፤ የልማት ስራዎች እዚህም እዚያም እየተፋጠኑ ቀጥለዋል፤ ኢትዮዽያም በልማት ወደ ፊት ግስጋሴዋን ተያይዛዋለች። የሀገሬ
ቀና መንገድ የማይታያቸው አንዳንድ ጨለምተኛ ፕሬሶችም በዳመነው ብዕራቸው ውሃ የማይቋጥር፤ እዚህ ግባ የማይባል፤የፍርሃት ፅሁፎቻቸውና
የኋልዮሽ መንገዳቸውን መምራታቸውን ቀጥለዋል። ይህን የእኔን ምልከታ የተጋሩና የተረዱ አንባብያን እስኪ ዛሬ ደግሞ ምን አሉ? ከማለት
ያለፈ ቁም ነገር የሚገኝባቸው የህትመት ውጤቶች እንዳልሁኑ ብዙዎቹ ግንዛቤ በመያዛቸው ትዝብት ውስጥ ማስገባታቸውን ለማከል እወዳለሁ።
የእነሱን የጥላቻ ወሬ በማንበብ ቤተሰቦቻቸውን የበተኑ፤ በውስጣቸውም ጥላቻን ያረገዙ ነበሩ። ሆኖም ለበርካታ ዓመታት ይዘት አልባ
ፅሁፎቻቸው ያመጡት ምንም አይነት መልካም ውጤት እንደሌለ በመረዳታቸው መንገዳቸውን አስተካክለዋል።
እነሱ ግን ዓላማቸው አንድና ያው ነውና ዛሬም አጧጡፈው ቀጥለውበታል።ምንም
እንኳ ብዙዎቻችን ከእነሱ የጨለምተኝነት አስተሳስብ የራቅንና የምናመዛዝን ብንሆንም እነሱ ግን በሀገርና ህዝብ ስም ስሜቶቻቸውን፤
ህልማቸውን፤ ቅዠታቸውን፤ ከመፃፍ አልቦዘኑም። ለዚች ምልከታዬም ባልበሰለ የብዕር ብትራቸው እንደሚወራጩ አውቃሁ። ከመንቃት ይልቅ
ባሉበት ሆነው እንደሚያቃትቱና እንደሚወራጩም ይሰማኛል። ግን ስሜቴን ሳይሆን ለዓመታት ያስተዋልኩትን ትዝብቴን በተሟላ መልኩ ባይሆንም
ለመጠቆም ሞክሬያለሁ ቀሪውን አንባቢዎቼ እንደሚሞሉት አልጠራጠርም።
እኔ ግን ዛሬም ሌላ ቀን ነው ለመለወጥ ጊዜ አላችሁ፤ ስለ መቻቻል፥ ስለ አንድነት፤ ስለ ሰላም፤ ስለ ፍቅር፤ ስለ ልማት፤
ስለ አብሮነት፤ ስለ አዲሲቷ ኢትዮዽያ፤ ስለ ብልፅግና፤ ስለ ታላቅነት፤ ብቻ እጅግ በርካታ ጉዳዮች ላይ መፃፍና ተነባቢነትን ማግኘት
ላቅ ሲልም ለሀገር ዕድገት እርሾ ማኖር ይቻላል ባይ ነኝ። አበቃሁ!!
No comments:
Post a Comment