Saturday, August 2, 2014

አክራሪነት ህገ-መንግስታችንን በመናድ ብዝሃነታችንን የሚደፍቅ የእኩልነታችን ጠንቅ ነው


የረድኤት ልጅ ሃኒ
ኢትዮጵያ የየራሳቸው ባህል እና ወግ፣ ታሪክ፣ እምነትና ሃይማኖት፣ ቋንቋና ወዘተ ያላቸው በርካታ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በመካባበር እና በመቻቻል የሚኖሩባት የብዙህነት ሀገር ናት።  የሀገራችን የብዙሃነት ምንጮች የአንድነታችን እና የጥንካሬአችን ምሶሶዎች በመሆን ከዘመን ዘመን አብረውን ተሻግረዋል። የውበታችንና የመቻቻላችን ምስጢሮችም ናቸው።  ይህ ዘመን ተሸጋሪ አብሮ የመኖር ሚስጢር ኢትዮጵያ ይዛው ከመጣችው ልዩና የመልካም ገፅታዎቿ እና መገለጫዎቿ አንዱና መሰረታዊው ሲሆን አለምን ያስደመመው አኩሪ ታሪኳም ነው፡፡

ኢትዮጵያ ከክርስቶስ ልደት በፊት ጀምሮ የሀይማኖት ብዝሃነትን ተቀብላና የሀይማኖት ብዝሃትን በአግባቡ ስታስተናግድ ኖራለች፡፡ ይህን ስንል በተለያየ የታሪክ ወቅቶች ይህን የብዝሃነትና የመቻቻል ባህል በመሸርሸር አብሮ የመኖር ወርቃማ ታሪካችን ጥላሸት የሚቀባ ክስተት አልተፈጠረም ተፈጥሮም አያውቅም ማለት ግን አይደለም። በተለያየ ወቅት አገሪቱን ያስተዳደሩ ቀደምት መሪዎች የብሄርና የሃይማኖት ብዝሃነትን በዴሞክራሲያዊ መንገድ ከማስተናገድ ይልቅ አንድ ጊዜ ብዝሃነትን በመደፍጠፍ ልዩነቶችን  በኃይል ለማስወገድ ሲጣጣሩ ይህ አልመች ያላቸው  ጊዜ ደግሞ ብዝሃነትን ከፋፍሎ በመግዛት እኩይ ስሌት ስልጣናአውን ለማራዘም እንደ መልካም አጋጣሚና መሳሪያ አድርገው ተጠቅመውበታል፡፡

ሀገራችን ኢትዮጵያ አንድ ሀገር፤ አንድ ቋንቋ፤ አንድ ሃይማኖት ወዘተ የሚሉ የተሳሰቱ አቅጣጫዎች እንደ ፖሊሲ  የተራመደባት፤ ብዝሃነት የአንድነቷ  አደጋ ተደርጎ የተሰበከባት እንዲሁም ተፈጥሮአዊ መገለጫዋ የሆነው ብዝሁነቷን  አደጋ ላይ የጣለ ጠባሳ ታሪክ  አሰልፋለች፡፡
በንጉሱ ዘመነ መንግስት (በ1948 ዓመተ ምህረት) በተሻሻለው ህገ-መንግስት አንቀፅ 126 ላይ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ-ክርስቲያን የንጉሰ ነገስቱ መንግስት መሰረታዊ ቤተ ክርስቲያን ናት በማለት በግልፅ ይደነግጋል፡፡ በዚሁ ህገመንግስት አንቀፅ 127 ላይ ህዝብና ካህናት ጳጳሳት ቢመርጡም ንጉሰ ነገስቱ ምርጫቸውን ካልተቀበሉና ሹመቱን ካልፈቀዱ መንፈሳዊ ስርዓት መፈፀም እንደማይቻል በማያሻማ ሁኔታ ያስቀምጣል፡፡ ከዚህ በግልፅ መረዳት የሚቻለው የንጉሱ ሀይማኖት የኦርቶዶክስ ሃይማኖት ብቻ መሆን እንዳለበት ይህም መንግስትና ሃይማኖት ፍፁም የተቀላቀሉ እና አንዱ የሌላኛው ማስፈፀሚያ መሳሪያ እንደነበረ  ነው ፡፡ እናም የሃይማኖቶች እኩልነትና የእምነት ነፃነት በሕገ መንግስት የተገደበበት ዘመን በመሆኑ የሃይማኖት ብዙሃነት ብሎ ነገር ፍፁም የማይታሰብ ነገር ነበር።
የይስሙላ የሃይማኖት ነፃነት የተከበረባት ሃገር ለማስመሰል ከወረቀት የዘለለ ትርጉም ያልተሰጠው ህገ- መንግስት ያፀደቀው አምባገነኑ የደርግስርዓትም በመሰረቱ ከንጉሱ ዘመን የተላየ ነገር መስራት የሚያስችል ፖለቲካዊ ቁመና አልነበረውም።አምባገነኑ የደረግ መንግስት በሃይማኖት ላይ ያለው አቋም አንደበቱና ድርጊቱ ፍፁም ያልተገናኙበት ነበር፡፡  የዓፈናና የጭቆና ስርዓቱን ለማራዘም ሲል ሃይማኖት ፀረ-አብዮት፣ ፀረ-ልማትና ጎታች የሆነ የአድሃሪዎች ተምሳሌት ነው በማለት  በግልፅ ፀረ ሃይማኖቶች ፖሊሲ ያራምድ ነበር፡፡     በህገ-መንግስቱ ላይ የኢትዮጵያ የህሊናና የሃይማኖት ነፃነት የተረጋገጠ ነው፣መንግስትና ሃይማኖት የተለያዩ ናቸው በሚል ቢያስቀምጥም ሃይማኖት የአድሃሪዎች መሳሪያ፣ ጎታችና የፀረ- አብዮት መሳሪያ ነው ብሎ ስለሚያምን የሃይማኖት ተቋማትን በማዳከም   የእምነት ተቋማት ጭምር የተዘጉበት ተከታዮቻቸውም ለእንግልትና ለስደት የተዳረጉበት አስከፊ ስርዓት እንደነበር የቅርብ ጊዜ ትውስታችን ነው፡፡
በአጠቃላይ ያለፉትን ስርዓቶች ስንመለከት  የሃይማኖት ብዝሃነትን እንደ የየስርዓቱ አደጋ ያዩበት በከፋፍለህ ግዛ እኩይ መርህ አንድን ሐይማኖት የበላይ ሌላውን የበታች በማድረግ፤ መንግስት የሃይማኖት አስተዳዳሪ አሊያም አደናቃፊ የሆኑበት፣ ሃይማኖቶችም በመንግስት ጉዳዮች ጣላቃ የሚገቡበት የመንግስትና የሃይማኖት መለያየት የሚባል ነገር ፍፁም የሌለበት ዜጎች የሚፈልጉትን ሃይማኖት በነፃነት ማራመድ ያልቻሉበት፤ ዜጎች ያለፈቃዳቸው የገዢዎችን ሃይማኖት  እንዲቀበሉ የተገደዱበት፤ የእምነት ነፃነት ብሎ ነገር የመሰይታሰብበት አስከፊ ስርዓት ነበር፡፡
ይህ ብዝሃነትን የማጥፋት ብሎም የህዝቦችን መብቶች በሀይልና በአስገደጅ ፖሊሲዎች የመጨፍለቅ አካሄድ ህዝቡን በመንግስት ላይ እንዲያምፅ አድርጓል፡፡ ተነግሮ የማያልቅ ክቡር መስዋትነት በመክፈልም ለብዝሃነትና ታቻችሎና ተከባብሮ ለመኖር አደጋ የሆነውን ስርዓት ላይመለስ በመጣል በአዲስ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት መተካት ችለዋል፡፡ አብሮ የመኖር የመቻቻልና ብዝሃነትን በማክበር የኖረበትን አኩሪና አለምን ያስደመመ ታሪካችንም ከጥፋት ማዳን ችሏል፡፡
ኢህአዴግ ገና ከጅምሩ መላውን የሀገራችንን ህዝቦች  በብሄር፣ በቋንቋ፣ ባህል፣ በዘር፣ በቀለም እንዲሁም በሃይማኖት ልዩነት ሳይደረግባቸው የእኩልነት መብታቸውና ነፃነታቸውን ለማረጋገጥ ታግሎ   ያተገለ ህዝባዊ ድርጅት ነው፡፡ ለእኩልነትና ለብዝሃነት የተሰለፈ ድርጅት እንደሆነም በትጥቅ ትግል ወቅት ሳይቀር በቀጣይነት ማስመስከር ችሏል፡፡ ከትግል በኋላም የኢትዮጵያ ሉዓላዊ የሥልጣን ባለቤቶች የአገሪቱ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች መሆናቸውን የሚያረጋግጥ ሕገ መንግስት ለማፅደቅ በተደረገው እልህ አስጨራሽ ትግል ከፍተኛ አስተዋፅኦ አበርክቷል።   በዚህ ሕገ መንግስትም ሁሉም ሰዎች ማንኛው ዓይነት ልዩነት ሳይደረግባቸው በሕግ ፊት እኩል መሆናቸውንና እኩል የሕግ ጥበቃ እንደሚደረግላቸው በግልፅ በማስቀመጥ የኢህዴግ ህዝባዊነት በቀጣይነት ተረጋግጧል። 

ኢህአዴግ በህዝቦች የተባበረ ክንድ የደርግን ስርዓት ከገረሰሰ በኋላ  ከታሪካችን የወረስነውን የተዛባ ግንኙነት በማረም የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች፣ የሃይማኖቶችና እምነቶች፣ የፆታና ማናቸውም እኩልነቶች በማረጋገጥ በኩልከፍተኛ መስዋእትነት በመክፈል ወርቃማ ስኬቶችን ማስመዝገብ ችሏል።  መንግስትና ሃይማኖት የሚለያዩበት ሴኩላር ስርዓት ለማረጋገጥ በከፍተኛ የኃላፊነት መንፈስ ተንቀሳቅሷል፡፡ሀገ-መንግስታዊ መሰረት እንዲኖረውም  የመንግስትና የሃይማኖት መለያየትን በህገመንግስቱ በግልፅ በመደንገግ ቁርጠኝነቱን በተግባር አሳይቷል፡፡

በኢፌድሪ ህገመንግስት አንቀፅ 27፣ አንቀፅ 25፣ አንቀፅ 11 ላይ ሁሉም ሃይማኖቶች በእኩል የሚታዩበት፣ የበላይና የበታች የሚባል ሃይማኖት እንደሌለ፣ ሃይማኖት በመንግስት መንግስትም በሃይማኖት ጉዳይ ጣልቃ እንደማይገቡ በግልፅ ተንግጓል፡፡   ዛሬ የሃይማኖት ተቋማት ያለገደብ በመስፋፋት ዜጎችም የአምልኮ ስርዓቶቻቸውንና አስተምህሮቶቻቸውን በነፃነት ማከናወን ችለዋል፡፡
መቼም  ቢሆን የኢትዮጵያን ሰላም የማይመኙና የያዘችውን የልማት ጎዳና ማደናቀፍ  ቀዳሚ ተግባራቸው አድርገው ለሚተጉ አንዳንድ አፍራሽ ሃይሎች በአንድ በኩል በብዙ መስዋዕትነት የተደፈቀው አስከፊ ስርዓት  ናፋቂና፣ የከሰረ ፖለቲካቸውን ለማራመድ ሲሉ ህገ መንግስቱንና ህገመንግስታዊ ስርዓቱን ለመናድ በሃይማኖት ሽፋን በአክራሪነትና በፅንፈኝነት ጎዳና ላይ ሽር ጉድ ሲሉ እያየን ነው፡፡ ይህ እንቅስቃሴአቸውም በማናቸውም መስፈርቶ ተቀባይነት የሌለው አ-ሕገ መንግስታዊ ድርጊት ነው።

የኢፌዴሪ ህገ-መንግስት አንቀፅ 11 መንግስትና ሃይማኖት የተለያዩ ናቸው፡፡ መንግስታዊ ሃይማኖት አይኖርም፡፡ መንግስት በሃይማኖት ጉዳይ ጣልቃ አይገባም፤ ሃይማኖትም በመንግስት ጉዳይ ጣልቃ አይገባም በማለት በማያሻማ መልኩ አስቀምጦታል፡፡

ስለሆነም በየትኛውም መንገድ መንግስታዊ ሃይማኖት ለመመስረት የሚደረግ እንቅስቃሴ ሁሉ ህገ-መንግስታችንን ለመናድ የሚደረግ እንቅስቃሴ ስለመሆኑ ማናችንም ብንሆን ብዥታ የለንም፡፡ መንግስታዊ ሃይማኖት በመደንገግ ወይም ሃይማኖታዊ መንግስት በመፍጠር ሌሎች ሃይማኖቶችን በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ለመደፍጠጥ የሚደረግ እንቅስቃሴ ተቀባይነት የሌለውና የእኩልነታችን ንቅ ከመሆኑም በላይ ኢሕገ መንግስታዊ የሆነ አፍራሽ አስተሳሰብ/ተግባር ነው።

አክራሪው ሃይል ኢትዮጵያ ውስጥ ሕገ መንግስቱ ካስቀመጠው አኳኋን ውጭ በድርድርም ይሁን ህገ-መንግሰቱን በመጣስ  መንግስታዊ ስልጣን መያዝ እንደማይችል ጠንቅቆ ሰለሚያውቅ ሃይማኖትን እንደ ሽፋን በመጠቀም የጎዳና ላይ ነውጥ እና ትርምስ መፍጠር በህጋዊ መንገድ ያጡትን ስልጣን በአቋራጭ በግርግር ለመቆናጠጥ የመቧዘኑ ምስጢር   ሀይማኖታዊ ሳይሆን ፖለቲካዊ እንደሆነ በገልፅ የሚታወቅ ነው፡፡ የአክራሪው ሀይል አማኞችም ሆነ ቅዠት የተለያዩ የማደናገሪያ የፈጠራ ወሬዎችን በማዘጋጀት የመእምኑን አስተሳሰብ በመስለብና በማታለል የኪራይ ሰብሳቢነት ፍላጎቱን ለማሳካት የሚያስችለው አፍራሽ ድርጊት ውስጥ ከተዘፈቀ ሰንበትበት ብሏል።

ይህ አክራሪው ኃይል በሕገ-መንግስቱ የተቀመጡ መሰረታዊ መርሆዎች የሚፃረር በመሆኑ ተቀባይነት የሌለው ኢ-ሕገ መንግስታዊ አስተሳሰብ/ድርጊት ነው ሲንል ማንኛውን ሰው የሚፈልገውን እምነት ለመያዝ ያለውን ነፃነት በኃይል በሌላ ሁኔታ በማስገደድ መገደብ ወይም መከልከል አይቻልም የሚለው ሕገ መንግስታዊ ድንጋጌ የሚጥስ በመሆኑ ጥምር ነው፡፡ ማንኛውም ሰው የመረጠውን ሃይማኖት ወይም እምነት የመያዝ ወይም የመቀበል ሃይማኖቱንና እምነቱን ለብቻ ወይም በግል ከሌሎች ጋር በመሆን በይፋ ወይም በግል የማምለክ፣ የመከተል፣ የመተግበር፣ የማስተግበር ወይም የመግለፅ መብትንም የሚንድ እኩይ ተግባር/አስተሳሰብም ነው አክራሪነት። የአክራሪነትና የፅንፈኝት ጫፍ ንፁሃን ዜጎችን አስተሳሰባቸውና አመለካከተቻው በጫና የመቀየር አካሄዱ ካልተሳካ ወደ ጅምላ ግድያ የሚሸጋገር ኢሰብአዊ ድርጊት በመሆኑ በማንኛውም መስፈርት ሃይማኖታዊ ተልዕኮ የሌለው እኩይ ተግባር/አስተሳሰብ ነው፡፡

ዜጎችን በመረጡትና በያዙት ሃይማኖት ምክንያት ለማሸማቀቅ መሞከር በኃይል ሃይማኖታቸውንና እምነተቻውን ለማስቀየር መንቀሳቀስ፣ የእኔ ሃይማኖት ካልተከተልክ በስተቀር አማኝ አይደለህም አሊያም ከሃዲ ነህ በሚል ማስፈራራትና አካላዊ ጥቃት ማድረስ፣ ግድያ መፈፀም የእምነት ተቋማትን ማፍረስ፣ መካነ-መቃብሮችን ማውደም፣ የሌላውን ሃይማኖት ማንቋሸሽ እና ማብጠልጠል ወ.ዘ.ተ የአክራሪነትና ፅንፈኝነት መገለጫዎች ሲሆኑ በሌላም በኩል ከሽብርተኝነት በቀጥታ የሚያያዙበት ዕድል ሰፊ ነው። ቹ ናቸው ከዚያ ሲያልፍም ሽብርተኝነት ነው ፡፡ በመሆኑም አክራሪነት ዜጎች የፈለጉትን እምነት የመያዝ ነፃነትን የሚደፈጠጥ ተቀባይነት የሌለው ኢ-ሕገ መንግስታዊ  ተግባር/አስተሳሰብ ነው፡፡ የሃይማኖት አክራሪነት በጥቅሉ የዜጎችን የሃይማኖትና እምነት ነፃነት በተግባር ለመናድ መንቀሳቀስ፤ የሃይማኖት እኩልነትን በተግባር ለመናድ መንቀሳቀስ፤ መንግስታዊ ሃይማኖት/ ሃይማኖታዊ መንግስት ለመመስረት የሚደረግ አፍራሽ እንቅስቃሴ ነው፡፡

አክራሪው ሀይል የሚፈፅማቸው  ድርጊቶች የዜጎችን ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ከመጣስም በላይ ድርጊቶቹ ሽብርተኝነት የሚመስል አካሄድ እየተከተሉ ነው ማለት ይቻላል፡፡
አክራሪው ኃይል እኩይ ተልዕኮውን ለማከናውን ወጣቶችን የዓላመውን ማስፈፀሚያ አድርጎ የሚንቀሳቀስ በመሆኑ ደግሞ ችግሩ ምን ያህል ፈታኝና አስከፊ መሆኑ መረዳት ይቻላል። አክራሪው/ ፅንፈኛው ሀይል የተለያዩ በሬ ወለደ ዓይነት የማደናገሪያ አጀንዳዎችንና አማላይ ዘዴዎችን በመጠቀም ወጣቶችን በዓላማ ማስፈፀሚያነት ለመጠቀም ያለየሌለ ዓቅሙ በመጠቀም እየተፍጨረጨረ ነው። ወጣቱን እየማገዱ ዳር ሆኖ እንደ መሞቅ ማለት ነው።

  ሀገራችን ለአመታት በአስከፊ ድህነቷና በርሃብ ምሳሌ በመሆኗ ምክንያት ዜጎች አንገታቸውን ደፍተው ቆይተዋል፡፡ ድህነቱም የሀገራችን የውርድትና የሀፍረት ምንጭ ነውና ከሰው በታች ሆን አቀርቅረን እንዲንኖርተገደን ነበር። በአሁኑ ውቅት ሀገራችን ይህን አስከፊና አወራጅ የድህነት ታሪክ ለማንኮታኮት በከፍተኛ ፍጥነት እየተንቀሳቀሰች ትገኛለች፡፡ በእርግጥም የፀረ ድህነት ትግሉ እየተጠናከረ በመሄዱ የሀገራችን የህዳሴ ጉዞ እየተፋጠነ ይገኛል።  ሀገራችን በሰላም፣ በልማትና በዴሞክራሲ ጎዳና ላይ በፍጥነት እየገሰገሰች ትገኛለች፡፡ የአክራሪዎች ዓላማ አልፋና ኦሜጋም ይህ በፍጥነት እየገሰገሰ ያለው ዕድገታችን በዕንጭጩ በመግታት ሀገሪቱ ለዓላማቸው የተመቸች ሆና እንድትኖር የማድረግ ትንቅንቅ ነው። በሌላ አገላለፅ የሀገራችን የህዳሴ ጉዞ በማሰናከል በድህነትና በኋላቀርነት አረንቋ ውስጥ ተዘፍቀን በከፍተኛ መስዋእትነት ትናንት ወዳለፍነው ድቅድቅ ጨለማ የመመለስ ተግባር ነው።

ኢትዮጵያውያንና የኢፌዴሪ መንግስት ግን ትላንት ያሳለፍነው አስከፊ ድህነትና ኋላቀርነት በአግባቡ እንገነዘበዋለንና ይህ ታሪክ ተመልሶ እንዲመጣ አንፈቅድም። በመሆኑም በአክራሪነትና ፅንፈኝነት ላይ የሚኖረን ትግል ለአፍታም ቢሆን የማይዘናጋ ከመሆኑም በላይ በአክራሪዎችና ፅንፈኞች የምንወስደው ሕጋዊ እርምጃም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተጠናከረ የሚሄድ ይሆናል። መንግስት በአክራሪዎችና አፍራሽ ኃይሎች ላይ ሕጋዊ እርምጃ በምወስድበት ወቅት ደግሞ አክራሪው ኃይል መንግስት በሃይማኖት ጉዳይ ጣልቃ እየገባ ነው፣ የእንትና ሃይማኖት ተደፈረ፣ የእንትና ሃይማኖት ነፃነቱ አልተጠበቀም፣ ሃይማኖትህ ተነካ ወዘተ እያለ ህዝቡን በቀጣይነት ለማደናገር ተግቶ በመስራት ይገኛል።

ይህ ዓላማው ለማሳካትም በውጭ የሚገኙ አፍራሽ ኃይሎች፣ በሕጉ መሰረት የተመዘገቡ ፅንፈኛ ተቃዋሚዎች እንዲሁም ንዳንድ አፍራሽ የግል የሕትመት ውጤቶች በቅብብሎሽና በቅንጅት የሚሰሩበት ሁኔታ በስፋት እየታየ ነው። አፍራሽ ሚዲያው እና በስመ ጋዜጠኝነት አሊያም በስመ ጦማሪነት እኩይ የሆነ የአክራሪነትና የሽብር ተግባር ሲፈፅሙ በመንግስት ቁጥጥር ስር በምውሉበት ወቅትም እንዲሁ በሀገሪቱ የፕሬስ ነፃነት አልተረጋገም፣ መንግስት ፕሬሶች እንዳይንቀሳቀሱ እያደረገ ነው በማለት መንግስትን ይወነጅላል። በተመሳሳይ ሁኔታ በአፍራሽ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ውስጥ ተወሽቀው የሽብር እና የአክራሪነት ግባር በመፈፀማቸው ምክንያት ብቻ በሕግ ቁጥር ስር በሚውሉበት ጊዜ መነግስት ተቃዋሚዎችን እያሰረ ነው፣ የተለየ ድምፅ መስማት አይፈልግም፣ መንግስት ፈርቷል ወዘተ በማለት የመንግስትን እርምጃ በቅብብሎሽ በማውገዝ ህዝቡን ለማደናገር ይፍጨረጨራሉ። ነገር ግን የፖለቲካ ፓርቲ አባል ወይም አመራር መሆን ከሕግ በላይ መሆን ማለት ስላልሆነ አሁንም በሕገ ወጥ ድርጊት ተሰማርተው እስከተገኙ ድረስ የፖለቲካ እምነታቸው ምን ይሁን ምን ከሕግ በታች ናቸውና ሕጋዊ እርምጃው ተጠናክሮ መቀጠል ያለበት ነው። መንግስትም የዜጎቹ ሰላምና ድህንነት የመጠበቅም የማስጠበቅም ሕጋዊ ግዴታ አለበትና ግዴታው በአግባቡ ለመወጣት በሕገ ወጦች ላይ ሕጋዊ እርምጃ መውሰዱ ተገቢም ትክክልም ነው እላለሁ።ነገር ግን ጋዜጠኛ ሆኖ ከሙያዊ ስነ ምግባር ባፈነገጠ መልኩ ሀገርን ለማተራመስ ከፅንፈኛውና ከሽብርተኛው ኃይል ጋር እጅ ጋንት ሆነው እስከሰሩ ድረስ በስመ ጋጤኛነት የሚከናወኑ ሕገ ወጥ ድርጊቶች በማንኛው መስፈርት ተቀባይነት የሌለው ተግባር በመሆኑ አሁንም እርምጃው ተገቢም ትክክለኛም ነው። ጋዜጠኝነትና ሀገር ማተራመስ ለየቅል ናቸውና። በአጠቃላይ የአክራሪዎችና የሽብርተኞች አካሄድ የተለያዩ ማደናገሪያ ስልቶችና ዘዴዎች እየተጠቀሙ ህዝቡን ከማታለል በተጨማሪ መንግስት በአጣብቅኝ ውስጥ በመክተት እጁ እና እግሩ አጣጥፎ እንዲቀመጥና ሀገሪቱ የእነሲ መፈንጫ እንዲትሆን በቅንጅት መስራት ነው። ይህም ዛሬም ሆነ ነገ በፍፁም ተቀባይነት የማይኖረው አፍራሽ ተግባር/አስተሳሰብ በመሆኑ ሁላችን በፅናት የምንታገለው ነው።


ለዘመናት አብሮን የኖረው  የመቻቻልና አብሮ በሰላም የመኖር ታሪካችን ለዓለም የምናበረክተው አኩሪ ቅርሳችን በመሆኑ ማንም ፅንፈኛ ሃይል ሊሰባብረው የማይችል በደማችን ውስጥ የሰረፀ የእኛነታችን መገለጫ ነው፡፡ ይህ ታሪካችንና ቅርሳችን ሁሌም በእኛ እንክብካቤ ውስጥ ሊሆንና ልንኮራበትም የሚገባ የሀገራችን ገፀ በረከትም ነው፡፡  አሁን ባለው የሀገራችን ተጨባጭ ሁኔታ ለአክራሪዎችም ሆነ ለሽብርተኞች መነሻ ሊሆን የሚችል የእኩልነት ችግር በመሰረቱ የተቀረፈ በመሆኑ አለየሚባል ልዩነት ካለም በሕጉ መሰረት ማስተናገድ የሚቻልበት ዴሞክራሲያዊ ስርዓት በተዘረጋበት ሀገር የኃይል እርምጃ በሙሉ ሕገ ወጥ ነው። ሕገ መንግስቱንና ሕገ መንግስታዊ ስርዓቱ ከሚደነግጉት ሁኔታ ውጭ ፖለቲካዊ ስልጣን በአቋራጭ ለመቆናጠጥ የሚደረገው የአክራሪዎችም ሆነ የአሸባሪዎች እንቅስቃሴም የህዝቦች ሉአላዊነት የሚያንኳስስ  ኢ-ሕገ መንግስታዊ ድርጊት/አስተሳሰብ በመሆኑ መቼም ቢሆን ተቀባይነት የመይኖረው ሕገ ወጥ ድርጊት ነውና ከህዝባችን ጋር በመሆን በቀጣይነት የምንታገለው ይሆናል። 

 የኢህአዴግ ድረ-ገፅ (www.eprdf.org.et) 


No comments:

Post a Comment