Tuesday, August 12, 2014

የሙስና ሊቀ ሊቃውንቶች

                                                                                                                                       ዮናስ
ፈረንጅኛው ሳይንቲስት እንዲል ሀበሽኛው ሊቀ ሊቃውንት ይለዋል፡፡ ስማዊ ልዩነቱ  እንደሃገራቸው ይሁን እንጂ ትርጓሜያቸው እና ገቢራዊ ፍቺያቸው ያው ነው፡፡ ሳይንቲስት  ይበሉት ሊቀ ሊቃውንት በመሰረቱ ሰው ነው፡፡ ሳይንቲስቶች እንበለውም ሊቀ ሊቃውንቶች  ሰዎች ናቸው፡፡ እኒህና ሊቀ ሊቃውንቶች የተባሉት ደግሞ በተሰማሩበት የስራ ዘርፍ  በተማሩበት የትምህርት ዘርፍና መሰል ማህበረሰባዊም ሆነ ሳይንሳዊ ኩነቶች ላይ የበቁ  የነቁ ያወቁ ግን ደግሞ ገና አልበቃንም፤ አላወቅንም ብለው ዘወትር የሚተጉ አይነቶች  ናቸው፡፡ በተለይ በእነዚህ ስያሜዎች የሚታወቁቱ እና መብቃታቸው በተግባር  የተረጋገጠላቸው ግለሰቦች ማወቃቸውና መንቃታቸው ከተወለዱበት፣ ካደጉበትና ከኖሩበት  ቀዬና ሃገር ባሻገርም ለአለም የተረፈላቸው መሆናቸውም እንዲሁ ግልፅ ነው፡፡ 

መብቃታቸውና ማወቃቸው ደግሞ በዋናነት ህዝብን ማዕከል አድርጎ ለህዝብ የሆነና  በየመብቃታቸው ደረጃ ያለውን የሰው ልጆች ችግር የሚፈታ፣ የችግሮች ሁሉ ቁንጮ  የሆኑትን የሚያስወግድና የተሻለና ለሰው ልጆች ምቹ የሆነችን አለም ለመፍጠር መደላደል
በሆኑ ስራዎቻቸውም የሚታወቁቱ ናቸው፡፡  በተለይ እንደኛ ባሉ ደሃ ሃገራት ያሉትን ዘርፈ ብዙ የሰው ልጆች ችግር ለማስወገድ የእነዚህ ሊቀ ሊቃውንቶች መብዛት የግድ መሆኑም እሙን ነው፡፡ የመልካም አስተዳደር  ችግር፣ የፍትህ እጦት፣ የህግ የበላይነት፣ ፍትሃዊ የሃብት ክፍፍል፣ የዋጋ ንረት፣ የኑሮ  ውድነት፣ የቤት ኪራይ፣ የትምህርት ክፍያ፣ የህክምና አገልግሎት፣ ጥራትና ዋጋ መናር 
አገልግሎት አሰጣጥ ወዘተ…እያልን የምንጮህላቸው ጉዳዮቻችን ሁሉ መነሻቸው በዚያም  ተባለ በዚህ ድህነት መሆኑ ላይ ልዩነት የሚኖረው አካል የለም፡፡

ስለሆነም ድህነትን ለማስወገድ በሚረዱ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንዲሁም ሳይንሳዊ፣ ባህላዊ ጉዳዮች ላይ ሁሉ የተለየ አይን የተለየ አፍንጫና የተለየ ጆሮ ያላቸው ጠቢባን  ያስፈልጉናል ማለት ነው፡፡ በእርግጥ ሁሉ ነገር ዜሮ ነው እያልኩ እንዳልሆነ ይታወቅ፡፡ ያም ሆኖ ግን ሃገራችን ያላትን የማይነጥፍ ሃብት መሰረት አድርገን ከድህነት  የምንወጣባቸው ስልቶችን ካበጀን ቆይተናል፡፡ የቆይታችንን ያህል ፍፁም ውጤታችን  ሚዛን አለመድፋቱም ግልፅ ነው፡፡ ለምን? ቢሉ ደግሞ ሊቀ ሊቃውንቶቻችን እና በውሰት  የምናመጣቸው ሳይንቲስቶቻችን፣ መነሻ የሚሆኑን ሳይንቲስቶች ወለድ መፅሃፍቶች  መሰረት ያደረጉት ሳይንሱ (ግብርናው ኢንዱስትሪው፣ ትምህርቱ ጤናው ወዘተ…)ላይ ብቻ  መሆኑ መሰረታዊ ይመስለኛል፡፡ ችግር ፈቺ ሊቀ ሊቃውንቶችን ባመረትን ቁጥር ችግር  ፈጣሪ ሊቀ ሊቃውንቶች መፈልፈላቸውም አይቀሬ መሆኑን የተገነዘብን አይመስለኝም፡፡  ስላልተገነዘብንም በማህበራዊ ዘርፎች ላይ በተለይ በግብረ ገብነት ሙያ፣ በሞራልና  በዜግነት ጉዳዮች ላይ በርካታ ሊቀ ሊቃውንቶች ሳናፈራ ቀርተናል፡፡ አፍርተን ከሆነም  ትንሽ ነው፡፡ ምክንያቱም ችግር ፈጣሪ ሊቀ ሊቃውንቶች በዝተዋልና፡፡ የዚህ ፅሁፍ መነሻ መብዛታቸውን በተጨባጭ ማሳያ ማመላከትና ከችግሩ የምንወጣበትን መንገድ መሻት  ነው፡፡ 

ድህነት መዋጋት የህልውና ጉዳይ መሆኑን ከተናገሩቱ እና ቃል ኪዳን ከገቡቱ ከፊሉ  ሂደቱን ለግል ህልውና መጠበቂያ ማዋላቸው ነው፡፡ ከላይ የተዘረዘሩትና ህዝብ የሚጮህባቸው ጉዳዮቻችን መነሻቸው ሙስና ነው፡፡ ሙስናን ለመታገል ሊቀ  ሊቃውንቶቻችን ያወጧቸው ህጎች የዘየዷቸው መላዎች እና እየሰጡ ያሉት ስልጠናዎች  ወዘተ…ግን መፍትሄ ያስገኙ አይመስሉም፡፡ በተለይ ከላይ ያሉትና የሙስና ተጋላጭ  በሆኑት አካባቢዎች የሚገኙ የስራ ኃላፊዎችና ግለሰቦች በአንድ ወቅት ሲያዙና ሲጋለጡ  እሰየው ብለናል፡፡ በእርግጥ ይህ አንዱ የመፍትሄ አካል ነው፡፡ ግን ደግሞ መፍትሄነቱ  እጅግም ስለመሆኑ ለመመስከር የትም ሳንሄድ ጠብ ያለ ነገር እንደሌለ አስተውለን  ለመናገር አይከብድም፡፡ 

ለምን ቢሉ የመፍትሄ መሰረታችንን እሴታችን በሆኑት የሞራልና የግብረ ገብ ጉዳዮች ላይ  አላደረግንምና፡፡ በገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን መስሪያ ቤት በየደረጃው የሚገኙ የስራ  ኃላፊዎች ተጠርጥረው ሲያዙ የፖለቲካ ልዩነት ነው ያሉ ቢኖሩም እነርሱም ማለታቸው  ለፖለቲካ ትርፍ ስለሆነ አልፈናቸው የሚበዛው ህዝብ ግን እሰየው ማለቱ የቅርብ ጊዜ  ሁነት ነው፡፡

ያም ሆኖ ግን እነዚህ በይፋ ተይዘው ይፋ ስለወጡ እንጂ በየለቱ በየመስሪያ ቤቱ የቅርብ  አለቆች እስከ ቅርብ ባልደረቦች የሙስና ሊቀ ሊቃውንቶች ሆነው በተለያየ መልኩ  ሲዘርፉና ሲመነደጉበት እንኳንስ ልንተነፍስ ‹‹ፕስስ መነጨቀ›› ብለን ማሞገሳችን እርግጥ  ነው፡፡ ጥያቄው ስለምን ነው ማሞጋገሳችን? ስለምንስ ነው ዝምታችን? የሚለው ነው፡፡ ያም  ይቅር በአንድ ወቅት ታምራት ገለታ በተባለ ‹‹ጠንቋይ›› ሊቀ ጠበብትነት የተጭበረበረውን  እና ሞራላዊ ክስረት የደረሰበትን ሁሉ አይተን ብዙ የተደነቅን ቢሆንም ነገርዬው  በአቋራጭ ለመበልፀግ ሳይለፋና ሳይሰራ ለማግኘት የሚሻ ህዝብ ባለቤት ስለመሆናችንም  ስናስተውል ባልተደነቅን፡፡ በዚህ ሊቀ ጠበብት የተደነቁቱ እና ያጨበጨቡትም ያው  ስለመሆናቸው ደግሞ የትም ሳንሄድ ከሰሞኑ ከአንዲት አፍሪካ ሃገር መጥቶ በሚለኒየም  አዳራሽ ገንዘብ ሊያበዛ እና ሀብት በሃብት ላይ የሚጨምር ፀበልና ዘይት እንዳለው  የተናገረውን ተከትለን መናኮራችንን እና አተርፍ ባይ አጉዳይ ሆነን መቅረታችንን  ያስተዋልን እንደሁ ነው፡፡

ሳሙኤል ዘሚካኤል የሚባለውን ቁጩ ዶክተርና ኢንጂነር የፈጠረልንም የኛ የሞራል  ደረጃና እሴታችንን መሰረት ያደረጉ ሊቀ ሊቃውንቶች በማጣታችን ነው፡፡ በአቋራጭ  የመበልፀግ ፍላጎታችንን ያሳየን የሳሙኤል አፈጣጠር ብቻ ሳይሆን በተጋለጠ ወቅት 
አድናቆትን መቸራችን እና መሰስ ብሎ ሲወጣ ዝም ያለው እና ይመለከተዋል ብለን  የጠበቅነው አካል ሁኔታም ነው፡፡ እርሱም ይቅር ሳሙኤል ብዙዎችን ማታለሉ እና  ሳይሰራ ሳይለፋ በብዚ ሺህዎች የሚቆጠር ገንዘብ መቀበሉም ይፋ ሆኗል፡፡ ግን ደግሞ በብዙሃን መገናኛ የሰማናቸው ግለሰቦች ህግ ፊት ቀርበው ሊመሰክሩና ክስ ሊመሰርቱ  ያለመቻላቸው ነገር ቢፈተሽ መቼም ይውሰደው አድናቂው ነን፤ ምንም አይጎዳንም ብለው እንደማይሆን አይጠረጠርም፡፡ ሚዛን የሚደፋው እና የሚጠረጠረው የዝምታ ግምት ከየት  አመጣኸው ሽሽትን ይመስላል፡፡ ወይም ስምና ዝናን ከሃገር ጥቅምና ከህግ የበላይነት  የማስቀደም ጉዳይ ነው፡፡ ከሁለቱ አይዘልም፡፡ ይህ ሁሉ ከየት መጣ ቢሉ ደግሞ  ከግብረገብና ሞራል ሊቀ ጠበብቶቻችን የሙስና ሊቀ ጠበብቶቻችን መብዛታቸው ነው፡፡ 

ሶማሊያ የምትባል ሃገር ስትነሳ ሁላችንም መቼም የትርምስ፣ የሽብርተኝነት መፈልፈያ  ስራ የማይሰራባት የተኩስ አውድማ መሆኗ ቀድሞ በጭንቅላታችን መምጣቱ አይቀርም፡፡  ሶማሊያ እንዲህ የሆነችው የጦርነት፣ የሽብርተኝነትና የትርምስ አራራ ስላለበት
የሚመስለው ካለ ተሳስቷል፡፡ ‹‹ትራንስፓረንሲ ኢንተርናሽናል›› የተባለ አለም አቀፍ  ተቋም በቅርቡ ይፋ ባደረገው ጥናት በአለም የሙስና ቁንጮ የተባለችው ሀገር ሶማሊያ  መሆኗን አረጋግጧል፡፡ የመልካም አስተዳደር እጦት ሽብርተኝነትና ህግን መገዳደርም ሙስና ወለድ የሆኑ ሁነቶች ስለመሆኑና ሙስና ሲከፋ የመንግስትን ህጋዊ ስልጣንም  በጉልበት እንደሚያስነጥቅ ሶማሊያ ጥሩ ማሳያ እንደሆነች ጥናቱ አመልክቷል፡፡ በርግጥም ትክክል ስለመሆኑና ሙስና ከጓዳ ወደአደባባይ ሊያውም በመንግስት መዋቅር 
አሰራር ላይ የመሸጋገሩን ሂደትና የሂደቱ ባለቤት ስለሆኑት የሙስና ሊቀ ሊቃውንቶች  አንድ ወዳጄ ሰሞንኛ ገጠመኙን ሲያወራኝ ማረጋገጥ ተችሎኛል፡፡ በዚህ ከቀጠለ ደግሞ በአዋጅና በእቅድ የምንሰራው ሽብርተኝነትን የመዋጋት፤ ሃሳብን በነፃ የመግለፅ የመናገር  ነፃት፣ የሃይማኖት እኩልነት፤ የብሄር ብሄረሰቦች መብት ውሃ እንደሚበላቸው የጓደኛዬ  ሰሞንኛ ገጠመኝ ሁነኛ ማረጋገጫዬ ሆኗል፡፡ 

ነገሩ እንዲህ ነው፡፡ (በነገራችን ላይ ‹ፀያፍ›› ገጠመኙን ያወጋኝ ጓዴ እየነገደና ነጋዴው  ከሚሆነውና ህጋዊ ከመሰለው የሙስና ሊቀ ሊቃውንቶቹ የአደባባይ ዝርፊያ አንፃር  እንደሃገሩ መሆን ግዴታዬ ነው ቢለኝም ቢያንስ ከሙስና ሊቀ ሊቃውንቱ ተግባር ተምሯል፤ ደግፏልምና ሁለተኛ ደረጃ ተጠያቂ ነው ለኔ፡፡ እኔም ሶስተኛ ተጠያቂ  እንዳልሆን ቢያንስ እንደሙያዬ ጉዳዩን አደባባይ እንዲውል መፃፌ ታሳቢ እንዲደረግልኝ) የእኒህ የሙስና ሊቀ ሊቃውንቶች ቦታ እና ነገርዬው የተከወነበትና እየተከወነ ያለበት ቤት 
ቁንጮዎቹን ይዘናል በተባለውና የነመላኩ ፋንታና ገብረዋህድ ቤት ከነበረው አንደኛው  ቅርንጫፍ መስሪያ ቤት ነው፡፡ አንደኛው ያልኩት ጓዴ ስላልነገረኝ ነው፡፡ (አለመናገሩ  በራሱም ተባባሪነቱን ወይም በዚሁ ተግባሩ የሚቀጥልበት እንደሆነ ያመላክታል) ቦታውን  በተለየ አልነገረኝምና ሊቀ ሊቃውንቶቹንም በስም እንደማይጠቅስልኝ አንባቢያን መቼም  አስቀድማችሁ እንደምትረዱኝ ግልፅ ነው) እዚህ ላይ ግልፅ ሆነን ወደ ሚስተር  ኤክሶቻችን፤ሊቀ ሊቃውንቶቻችን ድርጊት እንዲህ ስናመራ ከጓዴ የሥራ ዘርፍና የጉዳዩን  አፈጣጠር እንጀምራለን፡፡ 

የሙስና ሊቀ ሊቃውንቱ አባሪና ተባባሪ ወይም የወጉ ባለቤት የሆነው ጓዴ በምን ዘርፍ  እንደተሰማሩ ባላውቅም መርካቶ ከሚገኙ ሱቆች የተወሰኑቱ ባለቤት ለሆኑ ነጋዴዎች  የሂሳብ ባለሙያ እና ጉዳይ አስፈፃሚ ነው፡፡ ታዲያም በሆነው አይነት የንግድ ጉዳይ ላይ ሲፒኦ አሰርቶ በዚህና ሊቀ ሊቃውንቱ ባሉበት መስሪያ ቤት ማስገባት ነበረበትና  ያስገባል፡፡ እናም የንግድ ሰው እንዳለመሆኔ ሲፒኦ ተመላሽ የሚሆንበትን አግባብና የጊዜ  ገደብ ባልገነዘብም የተያዘው ሲፒኦ ጊዜ ገደቡ አልፎ ይሁን በሌላ እኔ በማላውቀው ግን ደግሞ ተገቢ በሆነ ምክንያት የሚቀርበትና ወደ መንግስት ገቢ የሚደረግበት እድል  ይፈጠራል፡፡ እንደመንግስት የተያዘው ሲፒኦ ወደመንግስት ገቢ የሚደረግበት ህጋዊ  አግባብ መኖሩን የተረዳው ጓዴ ሲፒኦው ይለቀቅለት ዘንድ የራሱን የንግድና እኔ የማላውቀው ምክንያቶች ይዞ አቤት ሊል የእነዚያን ሊቀ ሊቃውንቶች ደጅ መርገጥ ግድ  ይሆንበታል፡፡ ከሊቀ ሊቃውንቱ አንዱም ያለእርሱ ሊቀ ጠበብትነት በቀረበው አቤቱታ  መነሻነት አንዳች ነገር እንደማይፈጠር አስቀድሞ ያውቃልና ጉዳዩ እርሱን የሚመለከተው  ሆኖ ሳለ ጓዴ ወደሚፈልገው መስመር ይገባ ዘንድ ወደ በላይ አካል ይመራዋል፡፡ ጉዳዩ  ወደተመራበት ክፍል የሄደው ጓዴ ከበላይ ኃላፊዋ በምንም ምክንያት የተያዘው ሲፒኦ  የሚለቀቅበት ህጋዊ መሰረት እንደሌለ እና ችግሩም የራሳቸው የእነጓዴ መሆኑን ‹‹አሳምና›› ሸኘችኝ በማለት ወጉን ቀጠለልኝ፡፡ ስለሆነም የሙስናው ሊቀ ጠበብት  አመቻችቶ ለቆታልና ወደ እርሱ ለተመለሰው ጓዴ እስኪ ነገ ብቅ በልና እገሌን አናግር  ‹‹ይገባና አይገባ እንደሆነ ደውልልኝ ብሎ ስልክ ቁጥሩንም ጨምሮ ጓዴ በያዘው አቤቱታ  ሰነድ ላይ በ‹‹ስታይል›› አስፍሮ ህዝብ ተሰልፎ በሚጠብቅበት መስኮት ያቀብለዋል፡፡ ጓዴ ይኼኔ የሙስናው ሊቀ ጠበብትነት ገብቶታል፤ ለምዶትም ይሆናልና ምሽቱን ወደሊቀ ሊቃውንቱ ስልክ ይመታል፡፡ ከወዲያኛው መስመር ደግሞ ሲፒኦው ሊለቀቅ  የማይችልባቸውን አሳማኝና ህጋዊ አግባብነቶችን ያዳምጣል፡፡ ግን ሊለቀቅ የሚችልበትም  እድል እንዳለና እድሉም ያለው እዚሁና ቀን ያገኘው ሰው ላይ እንጂ ሌላ ጋር  አለመሆኑንም በስልኩ ይሰማል፡፡ አማራጩም ከባዶ የተሻለ እንደሚሆን ጓዴ እንደሚገነዘብ ልምድ የሚያውቀው ሊቀ ጠበብት የሀያ አምስት ሺህ ብር ሲፒኦውን ይወስድ ዘንድ  ወደመንግስት ገቢ የማይሆንበትን ምክንያት አበጅቶ ከምክንያቶቹም አንዱ የወሰደበትን  ቀን ወደ ኋላ ወስዶ በመፈረም በእጁ ላይ ይጥልለት ዘንዳ ጓዴ ደግሞ ሰባት ሺህ ብር  ለሊቀ ጠበብቱ ኪስ ማዋል ግዴታው እንደሆነ ተነገረው፡፡

በእርግጥም እንደአብዛኞቻችን እና ከላይ በተገለፁቱ በአቋራጭ የመበልፀግ ፍላጎቶቻችን  መነሻነት ወደፊቱን ሳይሆን የዛሬውን እንደሚያይ የሚጠበቀውና ከምንም አንድ  ሶስተኛውን መውሰድ የተሻለ እንደሆነ የተገነዘበው ጓዴ እሺ ሲል ይስማማና ጉዳዩ ሙስና  ጉቦ ነውና አፈፃፀሙን በተመለከተ ለሊቀሊቃውንቱ ጥያቄ ያቀርባል፡፡ እንደተለመደውና  እንድምንገምተው እዚህ ካፌ ወይም እዚህ ሆቴል ምናምን ጠብቀኝ ያለ  እንዳይመስላችሁ፡፡ የሙስና ሊቀ ሊቃውንቶች ስል ስያሜ መስጠቴም ለዚሁ ነው፡፡ ‹‹ሰባት  ሺህ ብርህን ይዘህ ጠዋት እንደማንኛውም ባለጉዳይ ተሰለፍ›› ብቻ ነው የሊቀ ሊቃውንቱ ትዕዛዝ፡፡ ስልኩ ተዘጋና ጓዴም እንዳወጋኝ ግራ በመጋባት በጠዋት ተራ ከሚጠብቀው  ባለጉዳይ እኩል ይሰለፋል፡፡ ከዚያም ይህ ፈፃሚ እንደየጉዳዩ ተገልጋዩን በመስኮት እየጠራ  የሚያስተናግደው በድርጀቱ ወይም በንግድ ስም እየጠራ ነው፡፡ እናም እንደባለጉዳዩ  አሰላለፍ የባለጉዳዮች ሰነድም ሰልፍ ይዞ ሊቀ ጠበብቱ እጅ ላይ ነውና የጓዴ ንግድ  ድርጅት ሲጠራ አቤት ይላል፡፡  ልብ በሉ እዚያው ሰልፍ በያዘበት ቦታ ላይ ሆኖ ነው አቤት ያለውና ነገሩም እየተፈፀመ  ያለው፡፡ አቤት አለ ጓዴ፡፡ ሊቀ ሊቃውንቱም ቲን ነበር አልተመዘገበም ይዘሃል? ኧረ  ረሳሁት በቃሌ ግን አውቀዋለሁ ሲልም ጓዴ ይመልሳል፡፡ ሊቀ ሊቃውንቱም በድንፋታ እና  በቁጣ እናንተ ደግሞ የተቀላጠፈ አገልግሎት እንዳንሰጥ የተሟላ መረጃ ይዛችሁ አትመጡ፤ ከዚህ በኋላ የተሟላ መረጃ ያልያዘ ወዘተ… ቀረርቶ ሲያሰማ አዳሜ ሰልፈኛ ያላሟላሁት ይኖር ይሆን ብሎ ቀልቡ ግፍፍ፤ ሀሳቡንም ወደራሱ ሰብሰብ ያደርጋል፡፡ ጓዴም ጉዳዩ  የሙስና ጨዋታው አካል እንደሆነ ወዲያው ገባውና (እዚህም ጋር ልምዱ እንዳለውም ሆነ  የሚቀጥልበት እንደሆነ አስቀድሜ መናገሬ) ባለአራት ይሁን ባለአምስት ዲጂት እርሱም  የማያስታውሳቸውን ቁጥሮች ጮክ ብሎ ይነግረዋል፡፡ 

ሊቀ ሊቃውንቱም በአቤቱታ ሰነዱ ላይ ቲን ነበሩን የሚፅፍ ይመስል አቀርቅሮ  እስኪሪብቶውን ወረቀቱ ላይ አንቀሳቀሰና፤ እንደገናም የደመረም የቀነሰም መሰለና ሰባት  ሺህ ብር ይክፈሉ ይለዋል፡፡ ጓዴም ሰባት ሺህውን ሊቀ ጠበብቶቹ በመንግስት የስራ 
ሰዓት፤ በመንግስት መስኮት፤ በርካታ ተገልጋይ ባለበት በማያስጠረጥር መልኩ ሙስና ላይ  ተጠበው ዘይደዋልና በይፋ ሰባት ሺህውን አስቀድሞ የተዘጋጀ እንዳይመስል እና እንዴትስ  ገምቶ እንዳይባል ከታሰረው አስር ሺህ ብር ላይ ሰባት ሺህ ቆጥሮ በመስኮት ለሊቀ ጠበብቱ ጀባ ሲለው፤ ምንም ከጉዳዩ ጋር ባልተያያዘ ሰነድ ላይ ጓዴን ያስፈርመውና  ሲፒኦውን ይቸረዋል፡፡ ጓዴም እየደነቀው በመሄድ ላይ ሳለ ከቆይታ በኋላ የሊቀ ሊቃውንቱ ስልክ ያቃጭልበታል፡፡ ጓዴም ምን አጎደልኩ ሲል እየተጨነቀ ስልኩን ሲያነሳ  ‹‹ብዙም አልተጨዋወትንም፣ እንግዲህ ሌላ ጊዜም እንገናኛለን፡፡ ፍትህ የተጠሙ እና  ፈጣን አገልግሎት የሚሹ ጓደኞችህንም ላካቸው እኛ መንግስት የጣለብንን አደራ  ለመወጣት ዝግጁ ነን፤ መልካም አስተዳደርና ፈጣን አገልግሎት በመፈክር እና በመግለጫ  ሳይሆን አብሮ በማደግ ተግባራዊ እንደሚሆን መገንዘብ ያስፈልጋል›› ብሎ ስልኩን ዘጋ፡፡  ጓዴም የመቀባበሉን ጨዋታ የለመደ ቢሆንም ያስገረመውና ለእኔ የመንገሩም ሚስጥር  በአደባባይ መስጠቱና ለዚህም የተበጀው ዘዴ ሳይሆን ቢያንስ ሆዳቸው የሚያውቀውን  ህገወጥ ድርጊት ህጋዊና ይልቁንም የመንግስት አደራ እንደሆነ ሊቀ ሊቃውንቱ ሳያፍር  ማውጋቱ ነው፡፡ እኔም ገርሞኝ ሳለ አንድ ደግሞ ልጨምርልህ አለኝና እንዲህ የሙስና  ሊቀ ጠበብቶችን ‹‹የጥበብ ደረጃ›› እንዲህ ይተርክልኝ ገባ፡፡ በነገራችን ላይ ከዚህና ከላይ  ከተመለከትነው ሊቀ ጠበብት ጋር ጓዴ ጓደኝነቱን እንደቀጠለና ሌሎችም አገልግሎት  የራቃቸው ጓዶች እንደሚልክለት ጭርሱንም መበዳደር እና መገባበዝ ደረጃ ላይ የደረሰ  ጓደኝነት እንደመሰረቱም አውግቶኛል፡፡ አደጋው እንዴት እየሰፋ እንደሚሄድ ልብ በሉ፡፡ ወደገጠመኝ ሁለት የጓዴ ትርክታችን እናምራ፡፡ ጓዴ የሚያማክራቸውና ከላይ ለተመለከተው ጉዳይ ባለቤት የሆኑት በንግድ ስራ ላይ  ተሰማርተው የሚገኙት ነጋዴዎች በጥምረት ደግሞ በሪል እስቴት ይሰማሩ ዘንዳ ጥናት  አስጠንተው አስፈላጊውን የጥምረት ውልና የህግ ስምምነት ከከወኑ በኋላ የከተማው አስተዳደር ለዚህ ዘርፍ ካዘጋጃቸው መሬቶች ስሙን ባልነገረኝ አካባቢ የሚፈልጉትን ካሬ  ስፋት መሬት ለሚመለከተው አካል ጥያቄ ያቀርባሉ፡፡ ዘርፉ እንደመበረታታቱ እና  እነርሱም አስፈላጊ የህግ ሰነዶችን እንደመያዛቸው ወደ ስራ ለመግባት ብዙም ጊዜ እንደማይወስድ የተገነዘቡት ተጣማሪ ባለሃብቶች ጓዴ እና ሁለት በሌላ የስራ መስክ  ለባለሃብቶቹ የምክር አገልግሎት የሚሰጡ ባለሙያዎች ባሉበት ተጣማሪዎቹ ላቀረቡት  የካሬ ስፋት ቦታ በአስተዳደሩ መረጃ መሰረት በጀት ለመያዝና ስለአፈፃፀም ሁኔታ ቃለጉባኤ ይዘው ውይይት ይቀመጣሉ፡፡ ቃለጉባኤ ያዡ ደግሞ የዚህ ወግ ባለቤት ጓዴ  ነው፡፡ 

እናም ባለው መረጃ መሰረት ላቀረቡት የመሬት ጥያቄ አምስት መቶ ሺህ ብር ቅድሚያ  መከፈል ስላለበት ያለምንም ተቃውሞና ክርክር በጀቱን ያፀድቃሉ፤ ግን ደግሞ  የተለመደው ተከፍሎም ወዲያው ወደስራ ለመግባት ለመንግስት ገቢ ከሚደረገው አምስት መቶ ሺህ ብር ከፊል ያህል ጉዳዩን ፈፃሚ ለሆኑት የመንግስት የሥራ ኃላፊዎች መግባት  ስላለበት፤ ሁሉም ቦታ ሊቀ ሊቃውንቱ አሉና ለእነርሱም የባለሃብቶቹ ጉባኤ በጀት መያዝ  ነበረበት፡፡ ያም ሆኖ ግን በግልፅና እነጓዴ ባሉበት አይሆንም፡፡ ግን ለስራቸው ቅልጥፍና  ሲሉ መሆንና በቃለ ጉባኤም መያዝ ነበረበትና ለጉቦ ሳይባል ለተለያዩ ጉዳይ ማስፈፀሚያ  እና ስራ ማስኬጃ የሚል ርዕስ ተሰጥቶት ሁለት መቶ ሃምሳ ሺህ ብር ይፀድቃል፡፡ በጥቅሉ  ሰባት መቶ ሃምሳ ሺህ ብር ይያዛል፡፡ ይህንንም ተከታትለውና ክፍያ ፈፅመው የመሬት ርክክብ ያደርጉ ዘንድ ጓዴን ጨምሮ የተቀሩት ሁለት አማካሪዎችን የባለሃብቶቹ ጉባኤ 
ይወክላል፡፡

ጉዳዩና በህግ አግባብ ያቀረቡት ጥያቄና በመንግስትም የመሬት ሰነድ ላይ ያለው አምስት  መቶ ሺህ ብር እንደሆነ በግልፅ የሚገነዘቡት ጓዴና ጓዶቹ ሁለት መቶ ሃምሳ ሺህው  ለምን እንደሆነ ስለገባቸው እነርሱም በተራቸው ሊቀ ጠበብት መሆን ይሹና እያንሰላሰሉ  ወደ ቢሮው ያመራሉ፡፡ በጥያቄያቸው መሰረት ሰነዳቸው እንዳለቀ እና ክፍያ ፈፅመው  መሬቱን መረከብ እንደሚችሉ የነገራቸው ሊቀ ሊቃውንት ስንት እንደያዙ ይጠይቃል፤ እዚያው በቢሮውና በግልፅ ሌላ አገልግሎት ፈላጊ ባለበትና ሌሎች ሰራተኞች ባሉበት፡፡  (ቢፒአር ተብሎ ሁሉ ነገር ፊት ለፊት መሆኑ ሙስናን ለመከላከል ሊቀ ጠበብቶቻችን  ያመጡትን ዘዴ ከእነርሱ የሚከፉት ሊቀ ጠበብቶች ደግሞ እንዲህ አደረጉት) እነ ጓዴ  በየድርሻቸው ሊቃረጡ እነርሱም አለቆቻቸው ላይ ሊቀ ጠበብት ሊሆኑ ቢሹም ስድስት  መቶ ሺህ በቂ እንዳልሆነ እና አሰራሩም የዋናውን ከፊል እንደሆነ በአለቆቻቸው መቼና 
እንዴት እንደሆነ ባያውቁትም እንደነገሩና መስማማታቸውንም ይገልፅላቸዋል፡፡ በዚህ ጊዜ  እርሱን ሳይሆን ማጋለጥ ቢፈልጉም አለቆቻቸውን እንደሚሆን እንዲያውም አስቀድሞ  የተሰጣቸውን ከመፈፀም የዘለለ ሚናም እንደማይኖራቸው የኃላፊው መልዕክት 
አረጋግጧልና ያለአንዳች አተካሮ እንደሚስማሙም ኃላፊው ያውቃልና፤ ጓዴ  እንደነገረኝም የኛም ሌላ መሻት በፈጠረው ክፍተት እንጂ አሰራሩ ስለሆነ ከሂሳብ ጋር  የተያያዘ ጥያቄ እዚያ አይነሳም፤ በማንሳታችንም አፈርን አለኝ፡፡ ከዚያም ሊቀ ሊቃውንቱ ሰባት መቶ ሺህ ብር ካሸሯ ጋር ክፈሉና ሪሲት ይዛችሁ ኑ ሲለን ደግሞ ዋጋው  ነው ብለን ተደናግጠን ልንሞግት ነበር፤ ምክንያቱ ደግሞ በሰነዱ የተመለከተው አምስት  መቶ ሺህ ብር ሆኖ ሳለ ሰባት መቶ ሺህ ብር ካሸሯ ጋር ክፈሉ ሊለን አይገባምና ብለን  ነበር፡፡ ያም ሆኖ ደግሞ የእነርሱ ጥበብ አያልቅምና የት ድረስም እንደሚረዝም ከልምድ  ተረድተናልና የተሰጠንን ሰነድ ይዘን ካሸሯ ጋር ገባን፡፡ ሰነዱን አይታ ምንም  እንልተፈጠረ ኮስተር ብላ እዚህ ላይ ፈርም አለች፡፡ ሰባት መቶ ሃምሳ ሺህ ብር ስትልም  አስከተለች፡፡ ቼኩን አስረክበን ደረሰኝ ሰራችና አስፈርማ ሰጠችን፤ ደረሰኙ ደግሞ አምስት  መቶ ሺህ ብር ነው የሚለው፡፡ ከዚያም የመንግስትን እዚያው በገዛ ሳጥኑ የሊቀ ሊቃውንቱን ድርሻ ደግሞ በየአካውንቱ ቼኳን መንዝራ በተን፤ በተን ነው ጨዋታው ሲል  አወጋኝ፡፡

ስለሆነም አሁን ጨዋታው በመንግስት ሰነድና በመንግስት ሰአት በአደባባይ እንጂ በስውር  ምናምን ለሰጪውም ለተቀባዩም የማይመች ሆኗል፤ ሌላውንም ለእስር የዳረገው ይኸው  እንደሆነ የተረዱት የሙስና ሊቀ ሊቃውንቱ ሌላ መላ ዘየዱና በገዛ በራሱ በመንግስት ቢሮ  ሙስና ላይ ተጠበቡ፡፡ ደረሰኙ አምስት መቶ ሺህ ብር ሰባት መቶ ሃምሳ ሺህ ብር ሰጠሁ፤ ብሎ ቢጮህ ደግሞም እኮ እንዴት ሊጮህ አለቆቹ ሰጥተውታል፤ ጠበብቶቹ የማህበረሰቡን  በአቋራጭ የመበልፀግ ፍላጎት ደረጃ ጠንቅቀው አውቀዋል፡፡ ታምራት ገለታ  የተጫወተበትን ህዝብ፣ ሁለተኛ አላሙዲ ተብሎ የመጣውና በአካውንቱ አምስት ሺህ ብር  ብቻ የተገኘው ግለሰብም ከምሁር እስከ ባለሃብት ከድምፃዊ እስከ ሞዴል ከዝነኛ እስከ  ምናምን ያሞኘውን ህዝብ፣ በልዩ የአቀራረብ ስልቱ በፋክት መፅሄት ላይ ‹‹የጎመጀ ህዝብ››  ሲል በብር አብዢውና በፈዋሹ ፓስተር የተሸወደውን የጎመጀ ህዝብ የኃይለጊዮርጊስ ማሞ 
ፅሁፍ ያጤነ ህዝብ፣ ለሳሙኤል ዘሚካኤል ኢንጂነር ወዶክተር ልዩ ብቃት ከሊቅ እስከ  ደቂቅ ከመዋእለ ህፃናት እስከ ከፍተኛ ተቋም ከምሁር እስከ ፕሮፌሰር ያጨበጨበና  ያልተጠራጠረ ህዝብ፤ የተገነዘቡት ሊቀ ሊቃውንቶች፡፡ ሙስና በቴሌቪዥን ድራማና  ማስታወቂያ ሊቀ ጠበብቶቻችን ፍልስፍና እንደማይገታ ቀድመው ተረድተዋልና  የሞራልና ግብረገብ ሊቀ ሊቃውንቶች ተፈልፍለው፤ ነገን የሚያስቡና የስራን ክብርና  ኃላፊነትን የተገነዘበ ትውልድ እስኪመጣ፣ ማታ አባቱ ያልዘራውን ሲያጭድ የሚያመሽ  ትውልድ እስካለ ሙስና ላይ ከዚህ በላይ ቢጠበቡም አይገርመንም፤ የሚያሳስበን ነገር ግን  አለ፡፡ ሶማሊያ የሆነችውን የሆነችው እንዲህ ባለ ሂደት ነው፤ ስለሆነም ከመግለጫ ከእስርና  ከማስታወቂያ የሚያላቅቁንና ማህበረ መሰረታችንን መሰረት ያደረጉ መፍትሄ  የሚያመጡልን ሊቀ ጠበብቶችን እንሻለን፡፡ 

No comments:

Post a Comment