Tuesday, August 5, 2014

ሕገ-መንግስታዊ ስርዓቱ በኃይል እንዲፈርስና ሕዝቡ በመንግስት ላይ አመኔታ እንዲያጣ ለማድረግ ተንቀሳቅሰዋል የተባሉ የኅትመት ውጤቶች ተከሰሱ

የዓመፅ ቅስቀሳና የሐሰት ወሬዎችን በመንዛት ሕገ-መንግስታዊ ስርዓቱ በኃይል እንዲፈርስና ሕዝቡ በመንግስት ላይ ያለአግባብ አመኔታ እንዲያጣ የሚያደርጉ ወንጀሎች ፈፅመዋል በተባሉ የኅትመት ውጤቶች ላይ ክስ መመስረቱን የፍትህ ሚኒስቴር አስታወቀ።

ሚኒስቴሩ "ሕገ-መንግስታዊ ስርዓቱን በዓመፅ ለመናድ የሚደረግ ሴራ መቆም አለበት" በሚል ርዕስ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት በላከው መግለጫ እንዳመለከተው ወንጀሎቹን በመሥራት በተጠረጠሩ አምስት መጽሔቶችና አንድ ጋዜጣ ላይ በአቃቤ ህግ ክስ ተመስርቷል።

በዚህም ፋክት፣ ጃኖ፣ ሎሚ፣ አዲስ ጉዳይና እንቁ የሚባሉ መጽሔቶች እንዲሁም አፍሮ ታይምስ የሚባለውን ጋዜጣ በሚያሳትሙ ተጠርጣሪ አሳታሚዎችና ድርጅቶች የአገሪቱ ህግ በሚደነግገው መሠረት ተከሰዋል።

ክስ የማቅረቡ ሂደትም በተደጋጋሚ ሕጉን በማንአለብኝነት በጣሱና በሚጥሱ አሳታሚዎችና የመገናኛ ብዙሃን ድርጅቶች ላይ እንደሚቀጥል መግለጫው አመልክቷል።
በህገ መንግስቱ የተቀመጡትን ገደቦች በመጣስ ብሄራዊ ደህንነትን አደጋ ላይ በሚጥል መልክ አመፅና ሁከት የሚቀሰቅሱ፣ አክራሪነትንና ሽብርተኝነትን የሚያወድሱና የሚያበረታቱ የኅትመት ውጤቶች መከሰታቸውን ገልጿል።

እነዚህንና በህዝቡ መካከል የዘርና የኃይማኖት ጥላቻን የሚቀሰቅሱ የህዝብ መሪዎችንና የተቋማትን መልካም ስምና ዝና በሃሰት የሚያጠፋና የሚወነጅሉ አንዳንድ ህትመቶች ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡም ሚኒስቴሩ አስጠንቅቋል።

አንዳንድ በኅትመት ዘርፍ የተሰማሩ የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎችና ድርጅቶች ሁኔታውን ከማሻሻል ይልቅ በየጊዜው የሚያደርጉትን የህግ ጥሰት በመቀጠላቸው ክስ ለመመስረት ማስገደዱን ገልጿል።

መንግስት የጨቅላውን የኅትመት ኢንዱስትሪ ልማት ለማጎልበት በማሰብ በዘርፉ የሚታዩ አንዳንድ ፅንፍ የወጡ ግድፈቶችን በህጋዊና አስተዳደራዊ ርምጃ ከማረም ተቆጥቦ ሁኔታውን በሆደ ሰፊነት ሲከታተል መቆየቱን መግለጫው አስታውሷል።
ራሱ የህትመት ሚዲያው ማህበረሰብ ችግሮቹን ለመቅረፍ የእርምት እርምጃ እንዲወስድ በተደጋጋሚ ሲያሳስብ መቆየቱንም አመልክቷል።

የጥቃታቸው ሰለባ የሆነው ሕዝብም በእነዚህ የኅትመት ውጤቶች የህግ ከለላ በተሰጣቸው ጥቅሞቹ ላይ ያለማቋረጥ የሚደሰውን ጥሰት ለማስቆም መንግስት ሕጋዊ እርምጃ እንዲወስድ በተለያዩ መንገዶች ሲጠይቅ መቆየቱን ነው በመግለጫው የተጠቀሰው።
የህግ የበላይነት የማስከበር ሃላፊነት ያለበት መንግስት ከክስ መለስ የተሻሉ ናቸው ያላቸውን አማራጮች አሟጦ በመጠቀም ህትመቶቹ ምግባራቸውን እንዲያርሙ ለማድረግ ያላሰለሰ ጥረት ሲያደርግ ቆይቷል።

''ሆኖም ግን አንዳንድ ሕትመቶች የመንግስትን ቻይነትና ትዕግስት ከመጤፍ ባለመቁጠር የሚፈፅሙትን የህግ ጥሰት አባብሰው ቀጥለዋል'' በማለት የኅትመት ውጤቶቹ ያሉበትን ሁኔታ ገልጿል።

መንግስት ሃሳብን በነፃነት የመግለፅ መብትን በማበረታታት በተለይም የግሉ የኅትመት ውጤቶች በዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ሂደት ያላቸውን የማይተካ ገንቢ ሚና በኃላፊነት ስሜት እንዲወጡ ተከታታይ የምክክር መድረኮች በማዘጋጀት ኢንዱስትሪውን መርዳቱንም አስታውሷል።

ይህንኑ በቀጣይ አጠናክሮ ለመቀጠል ያለውን ቁርጠኝነት በተደጋጋሚ ማረጋገጡንም አውስቷል።

ከህገ መንግስቱና ሕገመንግስቱን ለማስፈፀም በወጡ ህጎች የተበጁ ገደቦችን በማክበር ነፃነቱን ለመጠቀምና ለመተግበር የሚንቀሳቀሱ በርካታ ኃላፊነት የሚሰማቸው የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎችና ድርጅቶች መኖራቸውንም አስታውቋል።

መንግስት የህትመት ኢንዱስትሪውን ልማትና የስራ ነፃነት ለማጎልበት ከዘርፉ አካላት ጋር የጀመረውን አጋርነት አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጧል።


በአገሪቱ በማይቀለበስ ሁኔታ የተረጋገጠውን የመናገርና ሃሳብን በነፃ የመግለፅ እንዲሁም የሚዲያ ነፃነትን አድማስና ይዘት ለማበልፀግ በተጀመረው ጥረት ዙሪያ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ኃላፊነታቸውን እንዲወጡም ሚኒስቴሩ አሳስቧል።

ጭ፦ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት


No comments:

Post a Comment