Saturday, April 18, 2015

የኢንዱስትሪ ልማትን በማስፋፋት የአገራችንን ህዝቦች ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እየተጋ ያለ ህዝባዊድርጅት- ኢህአዴግ

የተከበራችሁ የአገራችን ህዝቦች
የኢንዱስትሪ ልማት በአገራችን ለዘመናት ተረስቶ የኖረና በተሳሳቱ የገዥዎች ፖሊሲዎች የተነሳ ለአገራችን እድገት ማበርከት ይገባው የነበረውን አስተዋፆ ሳያበረክት የቆየ ዘርፍ ነው፡፡ የቅርብ ጊዜውን እንኳን ብናይ የደርግ ስርዓት ይከተለው በነበረው የተዛባ ፖሊሲ ምክንያት አጠቃላይ ኢኮኖሚው ሲደቅ የኢንዱስትሪው ዘርፍ ደግሞ ይበልጡኑ መቀመቅ ውስጥ ገብቶ ነበር፡፡ በወቅቱ የነበሩት የአገሪቱ ጥቂትና ያረጁ ኢንዱስትሪዎች በመንግስት ቁጥጥር ስር በማስገባትም የግሉቁጥን ዘርፍ እንዲሽመደመድ አድርጓል። ይባስ ብሎም 500 ብር በላይ ካፒታል እንዳያካብቱና ከዛ በላይ የሆነ ሃብት ይዘው ቢገኙ ደግሞ በሕግ ተጠያቂ እንደሚሆኑ በግልፅ ሕግ ደንግጎ የኢንዱስትሪው ዕድገት ባለበት እንዲረግጥ አድርጓል።
በደርግ መቃብር ላይ የተገነባው የሀገራችን የነፃ ገበያ ስርዓት እውን መሆን በመጀመሩ የሀገራችን ኢንዱስትሪ እንዲያቆጠቁጥ አስችሏል።በአገራችን ለረጅም ዓመታት ሰፍኖ በቆየው የእዝ ኢኮኖሚ ሳቢያ ተገድቦ የቆየው የዜጎች በልማት የመሳተፍ መብት እንዲሁም ተነሳሽነት ማንሰራራት የጀመረውም በኢህአዴግ መሪነት በተቀየሰው የነፃ ገበያ ኢኮኖሚ አማካይነት ነው።
ኢህአዴግ በአገሪቱ የነፃ ገበያ ስርዓት እውን እንዲሆን በማድረጉ ኢንዱስትሪው እንዳያድግ ቀፍድደው ከያዙት የስርዓቶቹ ማነቆዎች ማላቀቅ ችሏል፡፡ይህ ብቻም ሳይሆን ልማት የህልውና ጉዳይ መሆኑን በግልፅ በማስቀመጥ አገራችንን ከድህነትና ኋላቀርነት ሊያላቅቁ የሚችሉና በህዝቡ ተሳትፎ የዳበሩ የተለያዩ ሀገር በቀል ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች ስራ ላይ ውለዋል፡፡ በወቅቱ አገራችን ያለችበትን ሁኔታ በጥልቀት በመተንተን ግብርናው የአገሪቱን ኢኮኖሚ እንዲመራ ሲደረግም አገራችን ያላት ሰፊ ሊለማ የሚችል መሬትና የሰው ሃይል እንዲሁም አነስተኛ ካፒታል እና ዝቅተኛ የቴክኖሎጂ አቅም በጥልቀት በማጥናት ነበር። በወቅቱ ምንም መሰረት ባልነበረውና የካፒታል እና የቴክኖሎጂ አቅማችን ውስን በነበረበት ሁኔታ ኢንዱስትሪው ኢኮኖሚውን እንዲመራው ቢደረግ ኖሮ ሁሉም የኢኮኖሚ ዘርፎች ከማቀጨጭ የተለየ ውጤት ማስመዝገብ እንደማይቻል የተረዳው ኢህአዴግ ለግብርናው ክፍለ ኢኮኖሚ ልዩ ትኩረት በመስጠት እንዲለማ ከረጅም ጊዜ አኳያ ደግሞ ኢኮኖሚው ወደ ኢንዱስትሪ እንዲሸጋገር ትክክለኛ አቅጣጫ አስቀምጧል፡፡
የተከበራችሁ የአገራችን ህዝቦች፤
ግብርና መር የኢንዱስትሪ ልማት ስትራቴጂ ሲቀረፅም ለግብርናው ዘርፍ ከተቀመጡለት ቁልፍ ተልዕኮዎች መካከል አንዱ ቀጣይነት ያለው የኢንዱስትሪ ግብዓት ማቅረብ ሲሆን ሌላው ደግሞ በግብርናው ዘርፍ የሚመዘገበው እድገት ለኢንዱስትሪ ምርቶች ሰፊና አስተማማኝ ገበያ መፍጠር ነው፡፡
በሌላ በኩል የከተማ ልማትና ኢንዱስትሪ ፖሊሲና ስትራቴጂ ሲቀረፅ በአንድ በኩል ለኢንዱስትሪ ልማት ምቹ ሁኔታ በመፍጠር በኢኮኖሚው መዋቅራዊ ለውጥ ማምጣትና አገራችንን ከበለጸጉት ሀገራት ጎን ማሰለፍ በዚሁ ሂደትም የብዙሃኑን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ፤ በሌላ በኩል ደግሞ ለልማታዊ ባለሀብቱ በተለይም ለአገር ውስጥ ልማታዊ ባለሀብት ቀጥተኛ ድጋፍ በመስጠት የኢኮኖሚ ልማቱ ዋና ሞተር እንዲሆን ማስቻል የሚሉ ሁለት መሰረታዊ አላማዎች ተቀምጠውለት ነው፡፡ በዘርፉ የተቀመጡት አቅጣጫዎችም የግብርና ግብዓቶችንና ጉልበትን በሰፊው በሚጠቀሙ፣ ከፍተኛ እሴት በሚጨምሩና ለኢንዱስትሪ ሽግግር ሁነኛ አስተዋጽኦ የማድረግ አቅም ባላቸው ቀላል ኢንዱስትሪዎች ልማት ላይ ትኩረት በማድረግ በግል ባለሀብቱ ተሳትፎ የማይሸፈኑ ነገር ግን ለኢኮኖሚው እጅግ ወሳኝ በሆኑ የተመረጡ ዘርፎች ላይ መንግስት ክፍተቱን የመሙላት ሚና የሚጫወትበት ግልፅ አቅጣጫ ተቀምጧል። በመንግስት የኢንዱስትሪዎች ንግድ ትኩረት በወጪ ንግድና ስትራተጂክ ገቢ ምርቶችን በመተካት ላይ የተመሰረተ እንዲሆን በማድረግ አለም አቀፍ ተወዳዳሪነት እንዲኖራቸው የመደገፍ ተልዕኮ እንዳለውና የአገር ውስጥ ባለሀብት የተሻለ የካፒታልና የቴክኖሎጂ አቅም ይዞ ከውጭ ከሚመጣው ባለሃብት ጋር በማስተሳሰር  በቴክኖሎጂ ሽግግር፣ በገበያ ትስስርና በዘመናዊ የማኔጅመንት አመራር አቅሙን ማሳደግ እንዳለበትም በግልፅ ተቀምጧል፡፡
በዚሁ መሰረትም የኢንዱስትሪ ልማቱን የሚደግፉ ፖሊሲዎች፣ ህግና ደንቦች፣ አደረጃጀትና አሰራሮች ተፈጥረዋል፡፡የመንግስት በጀትም ለኢንዱስትሪ ልማት ምቹ ሁኔታ በሚፈጥሩ መስኮች ላይ እንዲመደብ ተደርጓል፡፡በቀጣይነት ሰፊ ርብርብ የሚጠይቅ ቢሆንም የኢንዱስትሪ ልማት ፓርኮችንና የመሰረተ ልማት ግንባታዎችን በማሟላት የኢንዱስትሪ ኢንቨስትመንታችንን በማስፋፋትም ላይ ነን፡፡እነዚህ የኢንዱስትሪ መንደር ግንባታ ስራዎች በማጠናከርም በአንድ በኩል ኢንዱስትሪዎቹ የሚያስፈልጓቸው ድጋፎች በተማከለ ሁኔታ እንዲያገኙ በሌላ በኩል ደግሞ እርስ በራስ የሚኖራቸው ግንኙነት በማጠናከር ይበልጥ ውጤታማ እንዲሆኑ የሚያስችላቸው ነው።የኢንዱስትሪዎቹ የገበያ ሁኔታ በማመቻቸት ረገድም የኢንዱስትሪ መንደሮች የሚጫወቱት ሚና ከፍተኛ ነው።በእስካሁን አፈፃፀማችን አንዳንድ መንደሮች ወደ ስራ መግባት የጀመሩ ሲሆን ሌሎች ደግሞ በተለያዩ የግንባታ ደረጃዎች ይገኛሉ።በቀጣይም የኢንዱስትሪ መንደር ግንባታውን አጠናክረን በመቀጠል የሀገራችን የኢንዱስትሪ ጉዞ ለማሳለጥ ትኩረት ሰጥተን የምንሰራ ይሆናል።
ኢህአዴግ በዘርፉ የሚስተዋሉ ችግሮችን በመለየት፣ በተለይ ከልማታዊ ባለሃብቱ ጋር በመነጋገርና በመወያየት ችግሮቹ የሚፈቱበትን አግባብ ቀይሶ እየሰራ ይገኛል። የብድር አቅርቦት በማመቻቸት ረገድም ተመሳሳይ ስራ እየተከናወኑ ነው። ለረጅም ዓመታት ተዘንግተው የነበሩና በገበያ ሊሟሉ የማይችሉ የመሰረተ ልማት ክፍተቶችን የሚያሟሉ የመንገድ፣ የቴሌኮሙኒኬሽን፣ የኤሌክትሪክ ኃይል፣ የትራንስፖርት እንዲሁም የደረቅ ወደብና የኢንዱስትሪ ዞኖች እንዲሟሉና እንዲለሙ በመደረግ ላይ ናቸው፡፡
የከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ቁጥር 2 ወደ 34 ማደጉና ለኢንዱስትሪና ልማት ቀጣይነት ወሳኝ የሆነ የሳይንስና የኢንጂነሪንግ ባለሙያ የሰው ሀብት ማፍራት የሚያስችል አሰራር 70/30 መርሃ ግብር ተግባር ላይ መዋሉ ተጠቃሽ እርምጃዎች ናቸው፡፡ ምርትንና ምርታማነትን፣ የቴክኖሎጂ ሽግግርን በማሳደግ እንዲሁም ሰራተኛን በማሰልጠን ተወዳዳሪነትን ማሳደግ እንዲቻል ለግሉ ዘርፍ ድጋፍ የሚሰጡ ተቋማት በየንዑስ ኢንዱስትሪው ዘርፍ እንዲደራጁ በማድረግ ዘርፉን ተወዳዳሪ ለማድረግ እየተሰራ ይገኛል፡፡ ባለሀብቱ ብቃት ያለው ተወዳዳሪ እንዲሆን ለኢንዱስትሪ ኢንቨስትመንት የተዘረጉ ማበረታቻ ስርዓቶችም ተተግብረዋል። የእነዚህ ድጋፎች ድምር ውጤት ኢንዱስትሪውን ከግብርናና ከውጭ ንግድ ጋር በማስተሳሰር፣ የማጓጓዝና የሎጅስቲክስ ወጪዎችን በመቀነስ፣ ከፕሮጀክት እስከ ምርት ድረስ የሚወስደውን ጊዜ በማሳጠር ተወዳዳሪነትን የሚያሳድጉና የኢንዱስትሪያላዜሽን ጉዞአችንን የሚያፋጥኑ ናቸው፡፡
በኢንዱስትሪ ልማት እቅዳችን ውስጥ ወሳኝ ቦታ የተሰጠው ለአነስተኛና ጥቃቅን ተቋማች ነው፡፡ ይህ የሚሆነው በቅድሚያ በከተሞች ስራ እድል የሚፈጥው ዋና ዘርፍ  በመሆኑና የኢኮኖሚ ልማት እቅዳችንን አንድ መሰረታዊ ማጠንጠኛ የስራ እድል መፍጠር በመሆኑ ነው፡፡ ለእነዚህ ተቋሞች ቅድሚያ የምንሰጠው በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍም ቁልፍ የምርትና እድገት ተቋሞች ስለሆኑና መሆንም ለሚገባቸው ነው፡፡ ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ በገበያ የሚመሩ የከፍተኛና መካከለኛ ኢንዱስትሪዎችን የማልማት ስራችንን አጠናክረን ቀጥለናል፡፡ 
የተከበራችሁ የአገራችን ህዝቦች፤
ኢህአዴግ በአገሪቱ የነፃ ገበያ ስርዓት እውን እንዲሆን በማድረጉ፤ ትክክለኛ ሀገር በቀል ፖሊሲና ስትራቴጂ በመንደፉና ይህንንም ለማሳካት በቁርጠኝነት በመንቀሳቀሱ የኢንዱስትሪውን ዘርፍ ማስፋፋት ችሏል፡፡ ግብርናን መነሻ በማድረግ እየተፈጠረ ባለው ግብዓት ኢንደስትሪው በበቂ ክምችት ራሱን እንዲያጠነክርና በተመጋጋቢ ሁኔታ እንዲያድግ፣ ህዝባችንና አገራችንም ከዚሁ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ከልማት ወዳድ ህዝባችን ጋር በመሆንም ሌት ተቀን እየሰራ ይገኛል፡፡ ባለሀብቱ ከቀረጥ ነጻ በሆነ የፋይናንስ አተገባበር፣ በመሠረተ ልማት አቅርቦትና በአቅም ግንባታ ድጋፍ አግኝቶ ወደ ስራ እንዲገባ ድጋፍ በመደረጉ በዘርፉ የባለሃብቶች የልማት ተሳትፎ ከጊዜ ወደ ጊዜ መሻሻል እያሳየ ነው። ይሁንና አሁንም የባለ ሃብቱ ትኩረት ከማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ውጭ ባሉ የተለያዩ የልማት ዘርፎች ላይ በመሆኑ አሁንም ቢሆን ሀገራችን በዘርፉ ማግኘት የሚገባትን ጥቅም እያገኘት ስላልሆነ ቀጣይ ርብርብ የሚጠይቅ እንደሆነ ኢህአዴግ ይገነዘባል።   
የግል ባለሃብቱን ተሳትፎ በማጠናከር ወደ ተግባር የገባንባቸው የኢንዱስትሪ መስኮች በዓለም ገበያ በጥራት ለመወዳደር የሚያስችሉን ናቸው። በዚህም እስከ 2005 . 2655 መካከለኛና ከፍተኛ የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪዎች ተመዝግበው በእንቅስቃሴ ላይ ያሉ ሲሆን 2006 ዓመት ብቻ በመካከለኛና ከፍተኛ የማኑፋክቸሪንግ ኢንደስትሪዎች 341 የአገር ውስጥና የውጭ ባለሃብቶች ወደ ግንባታ ስራ ገብተዋል። አዳዲስ የጨርቃጨርቅና ስፌት ኢንዱስትሪ፣ የቆዳና ቆዳ ውጤቶች ኢንዱስትሪ፣ ብረታ ብረት ኢንዱስትሪ፣ ሥጋና ወተት ኢንዱስትሪ፣ የኬሚካልና ኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ፣ የፋርማሲቲካልስ ኢንዱስትሪ እና ምግብና መጠጥ ኢንዱስትሪዎችንም እንዲሁ መንቀሳቀስ የጀመሩበት ሁኔታ ተፈጥሯል። ዘርፉ የሚጠበቅበትን ውጤት እንዲያስመዘግብ ግን አሁንም ቀጣይ ርብርብ የሚጠይቅ እንደሆነ ኢህአዴግ ይገነዘባል።
ከኢንዱስትሪው ዘርፍ ውስጥም በተለይ በማኑፋክቸሪንግ የኢንዱስትሪ ዘርፍ የሚካሄደው ኢንቨስትመንት በሚፈለገው ደረጃ ዕድገት ባያሳይም ከጊዜ ወደ ጊዜ መሻሻል  እያሳየ ነው።በስራ ዕድል ፈጠራ ረገድም ጥቃቅንና አነስተኛ ኢንዱስትሪዎችን ሳያካትት የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ዘርፍ 2005 መጨረሻ ላይ 313,958 ሠራተኞች የስራ ዕድል የፈጠረ ሲሆን ከእነዚህ ዜጎች መካከል 75,099 (24 በመቶ) ሴቶች ናቸው፡፡  የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው ዘርፍም በስራ እድል ፈጠራ ካስገኘው የላቀ ጠቀሜታ ባሻገር በአገራዊ የኮንስትራክሽን የአቅም ግንባታና በቴክኖሎጂ ሽግግር ረገድ የማይተካ ሚና በመጫወት ላይ ነው፡፡
ኢህአዴግ በቀየሰው ትክክለኛ የኢንዱስትሪ ልማት ስትራቴጂ ለአገራችን ኢኮኖሚ መዋቅራዊ ሽግግር የተመቻቸ ሁኔታ የፈጠርንበትን የኢንዱስትሪ ልማት ግንባታ አጠናክረን ቀጥለናል። ዛሬ የኢንደስትሪው ዘርፍ የሀገሪቱን ነባራዊ ሁኔታ ማዕከል አድርጎ፣ የግብርና ምርትን በስፋት በግብዓትነት በሚጠቀሙ፣ ሰፊ ሰው ኃይል ሊሸከሙ በሚችሉ፣ የሀገሪቱን የቴክኖሎጂ አቅም ግምት ውስጥ ባስገቡና ለቴክኖሎጂ ሽግግር ምቹ በሆኑ ኢንዱስትሪዎች ላይ ትኩረት አድርጎ እየለማ ያለ ዘርፍ ነው፡፡ ባለፉት ሁለት አምስት የልማት ዕቅዳችን የኢንዱስትሪው ልማት ዘርፍ በጥቅሉ በየዓመቱ በአማካይ 10.9 በመቶ አኮኖሚያዊ ዕድገት ሊያስመዘግብ የቻለ ሲሆን የተመዘገበው ተከታታይ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት የሚሊኒየሙን የልማት ግቦች በማሳካትና ድህነትንና ኋላቀርነትን ለማስወገድ በሚደረገው ዘርፈ ብዙ እንቅስቃሴ የበኩሉን አስተዋጽኦ እያበረከተ ይገኛል፡፡ 
በዕድገት እና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዘመን ዘርፉን 10.6 በመቶ አመታዊ አማካይ ዕድገት ወደ 21.4 በመቶ ለማድረስ የታቀደ ሲሆን እስከ 2006. ያለው አፈፃፀም 20 በመቶ ዕድገት ማስመዝገብ ተችሏል፡፡ኢህአዴግ ለዘርፉ ምርታማነት ተገቢ ትኩረት ሰጥቶ በመንቀሳቀሱ የኢንዱስትሪ ምርት መጠን በሚፈለገው ደረጃ ውጤታማ ባይሆንም በቀጣይነት መሻሻል እያሳየ ምርቱ 2003 .  ከነበረበት 52.4 ቢሊዮን ብር 2006 . 87.7 ቢሊዮን ብር ከፍ ማድረግ ተችሏል። ከውጪ የሚመገቡ ምርቶችን በመተካትና የውጪ ምንዛሬን በማዳን ረገድም ይህ ከዜሮ ተነስቶ በማደግ ላይ ያለ ኢንዱስትሪ ትልቅ አስተዋፆ በማበርከት ላይ ይገኛል።
የተከበራችሁ የአገራችን ሕዝቦች፣
ኢህአዴግ ስትራተጂክ በሆኑና የገበያ ክፍተቶች በሚታይባቸው የሥራ መስኮች መንግስት ጣልቃ በመግባት የህዝባችንን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ ኢንደስትሪዎችን መገንባት እንዳለበት አጥብቆ ያምናል፡፡ በግል ባለ ሃብቱ የማይሸፈኑ ነገር ግን ለዕድገታችንና ለህዝቦች ተጠቃሚነት የሚያስፈልጉ ከፍተኛ ጠቀሜታ ያላቸው ምርቶችና አገልግሎቶች በመንግስት የልማት ትኩረት መሸፈን እንዳለባቸውም በፅኑ ይረዳል፡፡ ኢህአዴግ ማህበራዊ መሰረታችን ባልተቀየረበትና ሀገራዊ አቅም ባልዳበረበት ሁኔታ የመንግስትን ጣልቃ ገብነት መገደብ እንደኛ ባሉ አገሮች መሆን የሌለበትና የህዝባችንን በድህነት የመኖር ዕድሜ በእጅጉ እንደሚያስረዝም ይገነዘባል፡፡
መንግስት ካለው አነስተኛ ካፒታልም ቀንሶ ወደ ኢንቨስትመንት የገባው የግሉ ዘርፍ በተለያዩ ምክንያቶች ሊገባባቸው ያልደፈራቸውን ወይም ተሳትፎው አናሳ በመሆኑ ከፍተኛ የገበያ ጉድለት የሚታይባቸውን ዘርፎች ለመሸፈንና በዚህም የግሉን ዘርፍ ተሳትፎ ለማደፋፈር እንዲሁም የኢኮኖሚው ልማት የሚፈልጋቸውን ግብዓቶችና ትስስሮች ለመፍጠር ነው፡፡ እነዚህም በዋናነት የማዳበሪያ፣ የስኳር እንዲሁም የኢንጂሪንግ ኢንዱስትሪ ልማቶች ናቸው፡፡ በነዚህ አዳዲስ ኢንቨስትመንቶች የአገሪቱ የካፒታል ክምችት በቀጣይነት እያደገ የመጣ ሲሆን ከዘርፉ ምርት ጋር ሲነጻጸር 46በመቶ ድርሻ አለው፡፡
ከህዝቡ ፍላጎት በተፃራሪ የተሰለፉ በርካታ የሀገራችን ተቃዋሚዎች ግን ይህን እውነታ በመካድ መንግስት በምንም አይነት ሁኔታ ገበያው ውስጥ እጁን ማስገባት እንደሌለበት ይገልፃሉ፡፡ በኢህአዴግ የሚመራው  መንግስት ኃላፊነት በተሞላበት ሁኔታ የገበያ ጉድለት ባለባቸው ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ባላቸው ዘርፎች በመግባት የህዝቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ መስራቱንም ያጥላላሉ።
የልማታዊ አስተሳሰብ ባለቤት የሆነው ኢህአዴግ ግን በትክክለኛ አቅጣጫ በመጓዝ የግሉ ዘርፍ ሊሳተፍባቸው የማይችሉ ትልልቅ ኢንዱስትሪዎችን በመገንባት ለዕድገት ግንባታችን የበኩሉን አስተዋፅኦ በማበርከት ላይ ይገኛል፡፡ የገበያው ክፍተት እየተሞላ ከመጣባቸው ዘርፎች ደግሞ መንግስት እጁን ቀስ በቀስ ከገበያው እያወጣ ዘርፉ ለግል ባለሃብቶች እየለቀቀ አሁንም ትኩረቱ የግል ባለሃብቱ ወደማይገባባቸው ዘርፎች እያዞረ ይገኛል፡፡ ወደ ግል ይዞታ የተዛወሩ የተለያዩ ኢንዱስትሪዎችና አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ለዚህ ምስክር ይሆናሉ፡፡
ከመንግስት ወደግል ባለሃብት የተዘዋወሩ ኢንዱስትሪዎች አፈፃፀምም የአገር ውስጥ ባለሀብትን ተሳትፎ ለማሳደግ በሚያስችል አግባብ እየተፈፀሙ ናቸው፡፡ የአገር ውስጥ ባለሀብቶች ባለባቸው የካፒታል እጥረት ምክንያት ተሳትፏቸው በማነሱ የፖሊሲ ማሻሻያ በማድረግ የሽያጭ ዋጋውን 35 በመቶ ብቻ ከፍለው ድርጅቶችን እንዲረከቡ፣ ቀሪውን እየሰሩ የሚከፍሉበት ስርዓት በመዘርጋት ምቹ ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡ በዚህም በመንግሥት እጅ ከነበሩት የቆዳ፣ የጫማ፣ የጨርቃጨርቅ፣ የአልባሳት፣ የአገሮ-ፕሮሰሲንግ፣ የብረታብረታና ኬሚካል ኢንዱስትሪዎች ውስጥ አብዛኛዎቹ ለአገራዊ ባለሀብት ማስተላለፍ ተችሏል፡፡ በተለይ ለፋብሪካዎቹ ግብዓት አቅራቢ የነበሩ ነጋዴ ባለሀብቶች ፋብሪካዎቹን በመግዛት ወደአምራችነት ተሸጋግረዋል፡፡ እስከ 2006 . መጨረሻ ድረስ 370 ድርጅቶች ወደ ግል ይዞታ የተዘዋወሩ ሲሆን ከዚህ ውስጥ አገራዊ ባለሀብቶች 87 በመቶ ሙሉ ለሙሉ በመግዛት፣ 10 ደግሞ ከውጭ ባለሀብት ጋር በመቀናጀት የፕሮግራሙ ዋና ተጠቃሚ መሆን ችለዋል፡፡
የተከበራችሁ የአገራችን ህዝቦች፣
ኢህአዴግ በትክክለኛ ሀገር በቀል ፖሊሲዎቹና ስትራቴጂዎቹ እየተመራ በኢንዱስትሪው ዘርፍ ውጤቶች ማስመዝገብ የቻለው በፈተናዎች ውስጥ እያለፈ ነው፡፡ፈተናዎች ሲያጋጥሙት እንደየአግባቡ መፍትሄ እያበጀ፣ ከድክመቶቹ እየተማረ በመሄዱ አሁን ላለበት ደረጃ መድረስ ችሏል። አሁንም ዘርፉ ገና ያልተፈቱ ችግሮች እንዳሉትና አገራችን ከዘርፉ ማግኘት የሚገባትን ጥቅም ለማግኘት ቀጣይ ርብርብ እንደሚያስፈልግ ኢህአዴግ ይገነዘባል። በዚህ ረገድ ከሚያጋጥሙት ፈተናዎች ችግሮች መካከል የግል ባለሃብቱ በተለይ የአገር ውስጥ ባለሃብቱ በአምራች ኢንዱስትሪዎች ያለው ተሳትፎ ዝቅተኛ መሆን፣ የወጪ ንግድ በሚፈለገው ደረጃ ያላደገ መሆኑና የካፒታል እጥረታችን አሁንም ያልተቀረፈ መሆን ይገኙበታል፡፡ ኢህአዴግ እንደ እስከዚህ ቀደሙ ሁሉ በኢንዱስትሪው ዘርፍ ያሉ ማነቆዎችና ፈተናዎች  ለመፍታት ከመላ የሀገራችን ህዝቦች እና ከልማታዊ ባለ ሃብቱ ጋር እጅ ለእጅ ተያይዞ ይሰራል።
በመሆኑም ለሀገራዊ ህዳሴያችን መረጋገጥና ለህዝቦች የላቀ ተሳትፎ መረጋገጥ ብሎም የተጀመረው የልማት ውጥን ዳር እንዲደርስ ኢህአዴግን ይምረጡ!
ኢህአዴግን መምረጥ ነጻ ውድድርን የሚያሰፍን፣ ማህበራዊ ልማትን የሚደግፍ፣ የአካባቢ ተጽእኖን የማያስከትል አረንጓዴ  የኢንዱስትሪ ዕድገትን በማረጋገጥ ቀጣይነት ያለው የኢንዱስትሪ ልማትን ማረጋገጥ ማለት ነው፡፡


No comments:

Post a Comment